Master mind2015
"አሐተ ፡ ሰአልክዎ ፡ ለእግዚአብሔር ፡ ወኪያሃ ፡ አኀሥሥ ፤
ከመ ፡ እኅድር ፡ ቤቶ ፡ ለእግዚአብሔር ፡ በኵሉ ፡ መዋዕለ ፡ ሕይወትየ።"
እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንኩት እሷንም እሻለሁ።
በሕይወት ዘመኔ ሁሉ በቤቱ እኖር ዘንድ።
06/03/2026
➻🦋 🦋➻
✝️አደመጥሁ ሰማሁም፣ቅንን ነገር አልተናገሩም፣
ማናቸውም ምን አድርጌአለሁ?ብሎ ከክፋቱ ንስሐ የገባ የለም፣ወደ ሰልፍም እንደሚሮጥ ፈረስ እያንዳንዱ በየመንገዱ ይሄዳል።”ኤርምያስ 8፥6።ነብያትም መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስም፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ፣ሐዋርያትም፣ጻድቃን ሰማእታትም ሁሉም የትምህርት ወንጌላቸው መጀመሪያ ንስሐ ግቡ ነው የሚሉት ንስሐ ማለት:__ጸጸት ነው ፣ መቆጨት ነው ፣ ንስሐ ማለት በደልን መተው ነው ፣ ሰው ንስሐ ካልገባ ወደ እግዚአብሔር መንግስት አይገባም ። ወደ እግዚአብሔር መንግስት ለመግባት ንስሐ መግባት ያስፈልጋል።ስጋ ለብሶ የማይበድል የለም። ልብስ በሳሙና ፣በኦሞ ፣ በእንዶድ ይታጠባል ።ይህ የልብሳችን እድፍ ለማጠብ ነው እንግዲህ ለልብሳችን ውሀ፣ለኃጢአታችን ንስሐ ተዘጋጅቶአል። ስለዚህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ይል ነበር ። በማቴ 4÷17//ላይ። "በማቴ 3÷1-2//ላይም መጥምቁ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ንስሐ ግቡ ይል ነበርን ።ስለዚህ ንስሐ መግባት አስፈላጊ ነው ። ያልገቡት ደግሞ ምን አድርጌአለሁ ብሎ ንስሐ አልገቡም ይላል ይህ የወቀሳ ቃል ነው ። ወደ ትምህርታችን መለስ ብለን ንስሐ መግባት ያስፈልጋል ። በህጻንነታችን አንስቶ፣ በወጣትነታችን አንስቶ፣ በሽምግልና በባልቴትነት ፣ ሴትና ወንድ ጾታ ሳንለይ :_እግዚአብሔር ያስቀየምን ፣ ሰው ያስቀየማች ፣ሰው የገደላችሁ ንስሐ መግባት ያስፈልጋል ። መጸጸት. ያስፈልጋል ። ይቅርታ መጠየቅ መልካም ነው ። ማረኝ ፣በድያለሁ፣ አስቀይሚያለሁ ማረኝ ማለት ተገቢ ነው ።
✝️“ ከክፋቱ ንስሐ የገባ የለም፤ ወደ ሰልፍም እንደሚሮጥ ፈረስ እያንዳንዱ በየመንገዱ ይሄዳል”ኤርምያስ 8፥6
ማቴዎስ 21÷28//ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት።ወደ አንደኛው ቀርቦ፦ ልጄ ሆይ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ አለው።እርሱም መልሶ፦ አልሔድም አለ። ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ። ይህ ማለት በፊት አልሄድ ብሎ እንቢ አለ በኃላ ግን ተጸጽቶ ሄደ ማለት ተጸጽቶ ንስሐ ገባ ማለት ነው ። ሁለተኛው ደግሞ:ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው እርሱም መልሶ፦ እሺ ጌታዬ አለ፣ ነገር ግን አልሄደም። ለጊዜው እሽ ብሎ አለመፈጸሙ ንስሐ አለመግባቱን ይነግረናል ። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው? ፊተኛው አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ እውነት እላችኋለሁ፣ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል።ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ መጥቶላችሁ ነበርና፥ አላመናችሁበትም፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ግን አመኑበት፤ እናንተም ይህን አይታችሁ ታምኑበት ዘንድ በኋላ ንስሐ አልገባችሁም።
✝️ይህ ወቀሳ ጻፎችና ፈሪሳውያን የአይሁድ ካህናትን ይመለከታል። ቃሉን ተምረው ለሌሎች እያስተምሩ፣ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ንስሐ ግቡ እያለ ሲያስተምር ንስሐ አልገቡ። ለዚህ ነው ምን አድርጌ ይሁን ብለው ተጸጽተው ንስሐ አልገቡም የሚለን ። ንስሐ መግባት አስፈላጊ ነው ። ንስሐ መግባት ተገቢ ነው ከተጠያቂነት ያድናል ። እንዲህ ይላል፦
06/03/2026
🕎🍀 🍀🕎
✅ኢትፍርህዎ ለሞት ፍርህዋ ለኃጢአት ቅዱስ ያሬድ ሞት በብዙ መንገድ ቢተረጎምም ቀጥተኛ የቃሉ ፍቺ ግን መለየት ማለት ነው፡፡አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በሚል መጽሐፋቸው“መሞት፣ መለየት፣ በነፍስ ከሥጋ፣በሥጋ ከነፍስ መራቅ፣እየብቻ መኾን፣ መድረቅ፣ መፍረስ፣ መበስበስ፣ መነቀል፣ መፍለስ፣ መጥፋት፣ መታጣት” በማለት ይፈቱታል፡፡ (ኪዳነ ወልድ፣ገጽ፣፭፻፹፩) እንዲሁም አለቃ “ሞት በቁሙ የሥጋዊና የደማዊ ሕይወት ፍጻሜ በአዳም ኃጢአት የመጣ ጠባይዓዊ ዕዳ ባሕርያዊ ፍዳ”በማለት ይፈቱታል፡፡ (ዝኒ ከማሁ) ከላይ በተገለጸው ገጸ ንባብ እንደምንረዳው ሞት አንድ ላይ የነበሩ አካላትመለያየት ለየብቻ መሆን፣ መራራቅ፣ ወዘተ ማለት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ሞትን በአጭር አገላለጽ እንዲህ ነው ብሎ መተርጎም ከባድ ስለሚሆን በዓይነት ከፋፍለን ለመመልከት እንሞክራለን፡፡
✅ሞት ከላይ በተመለከትነው መልኩ መለየት፣ በሥጋ ከነፍስ መራቅ፣ እየብቻ መኾን ማለት ሲሆን በዋናነት ሞተ ሥጋና ሞተ ነፍስ ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡
ሀ. ፡- የሥጋ ሞት የሚባለው የነፍስ ከሥጋ መለየት ማለት ነው፡፡ ይህ ሞት የማይቀር ስለሆነ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “ኢትፍርሕዎ ለሞት ፍርሕዋ ለኃጢአት እስመ ሞትሰ ኢየኀድገክሙ ዘበላዕሉ ኀልዩ ወአኮ ዘበምድር፤ ሞትን አትፍሩት ኃጢአትን ግን ፍሩ ሞት አይቀርምና ስለሰማያዊው አስቡ እንጂ ስለምድራዊው አይደለም” እያለ ያስተምራል፡፡ ስለዚህ ሞተ ሥጋ ሲባል በተዋሕዶ አንድ ሁነው የኖሩት ነፍስና ሥጋ መለያየት ለየብቻ መሆን ማለት ነው፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ሃይማኖትና ምግባር የማይነጣጠሉ እንደሆኑ በምሳሌ ሲያስተምር የጠቀሰው የነፍስና የሥጋን ህልውና ነው። «ከመ ሥጋ ዘአልቦ መንፈስ ምውት ውእቱ ከማሁ ሃይማኖትኒ እንተ አልባቲ ምግባረ ሠናይ ምውት ይእቲ ለሊሃ፤ ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው» (ያዕ.፪፥፳፮) እንዲል፡፡ ስለዚህ ነፍስ ያለሥጋ ሥጋም ያለ ነፍስ ህልውና አይኖራቸውም። ይህ ማለት በሰውነት ህልውና እንጂ ነፍስና ሥጋ ተለያይተው ነፍስም በገነት ወይም በሲኦል ሥጋም በመቃብር አይኖሩም ማለት አይደለም፡፡ በመሆኑም የሥጋ ሞት የሚባለው የነፍስ ከሥጋ መለየት ነው። ይህ የነፍስ ከሥጋ መለየት የጻድቅ ከሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ነው።
ለ. ፡- የነፍስ ሞት ማለት የነፍስ ከእግዚአብሔር መለየት ማለት ነው፡፡ የነፍስ ከእግዚአብሔር መለየት በሁለት መንገድ ወይም ወቅት ሊከሠት ይችላል፡፡ የመጀመሪያው ገና ነፍስ ከሥጋ ሳትለይ ወይም በአጸደ ሥጋ ሳለ ኃጢአት በመሥራት የሚፈጠረው ከእግዚአብሔር መለየት ነው፡፡ አባቱን ቀብሮ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሊከተል ጥያቄ ያቀረበውን ደቀ መዝሙር “ሙታኖቻቸውን ይቀብሩ ዘንድ ሙታንን ተዋቸው፡፡(ማቴ.፰፥፳፪) በማለት ነፍሳቸው ከሥጋቸው ሳትለይ ኃጢአት ሠርተው ከእግዚአብሔር የተለዩት (ሙታን) ነፍሳቸው ከሥጋቸው የተለችባቸውን ሙታን ይቅበሯቸው ብሎ አስተማረ፡፡
✅ነፍስ በባሕርይዋ የምትሞት አይደለችም፤ ሞተ ነፍስ የሚባለው የማትኖርበት ጊዜ ስላለ ሳይሆን ከምትኖርበት ሁኔታ አንጻር ነው። ይህ ማለት ነፍስ በሃይማኖት ጸንታ በምግባር ቀንታ ባለመኖሯ ወደ ሲኦል በኋላም ገሃነመ እሳት ትወርዳለች። የነፍስ ሞት ማለት ገነት በመግባት ፈንታ ሲኦል፣ መንግሥተ ሰማያት በመግባት ፈንታ ገሃነመ እሳት መግባት ነው። «ድል የነሣው ሁለተኛውን ሞት አያይም (ራእ.፪፥፲፩) ተብሎ የተጻፈው ነፍስ ከሥጋ መለየትን ሳይሆን ገሃነመ እሳት መውረድን አያይም ለማለት ነው።ሞት ማለት መለየት ነውና ነፍስ ከፈጣሪዋ ከእግዚአብሔር ተለይታ ካልፈጠራት ከዲያብሎስ ጋር መኖር ስትጀምር የነፍስ ሞት ይባላል። ሁለተኛ ሞት የተባለውም እግዚአብሔር ያዘጋጀውን መንግሥተ ሰማያት አጥታ በኃጢአቷ ምክንያት ገሃነመ እሳት መውረድ ነውና«ድል የነሣው ሁለተኛውን ሞት አያይም»
ማለት ከላይም እንደተገለጸው ገሃነመ እሳት አይገባም ማለት ነው።ከላይ ለተመለከትናቸው የሥጋም ሆነ የነፍስ ሞት ልዩ ልዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡
ሀ.ተፈጥሮ፡- እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥር የስሙ ቀዳሽ፣ የመንግሥቱ ወራሽ ሁኖ እንዲኖር ነው፡፡ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረው የሰው ልጅ ትእዛዙን ጠብቆ ለጊዜው ይኖርባት ዘንድ ከተሰጠችው ከገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዲሸጋገር ነው፡፡ ይህ ከገነት የሚሸጋገርበትም መንገድ ዕፀ ሕይወትን በልቶ ታድሶ ነው፡፡
✅ይህ ሞት ዕፀ በለስን በልቶ ከእግዚአብሔር በጸጋ ያገኘውን ከተነጠቀ በኋላ ሥቃይ የበዛበት ሁኗል፡፡ በተለይም ከውድቀት በኋላ እስከ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ድረስ የከፋ ነበር፡፡ ሰው ሁሉ በጻእር፣ በጋር፣ በጭንቅ ይሞት ነበር፡፡ ሞቶም ወደ ሲኦል ይወርድ ነበር፡፡ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት “ሕያው ሁኖ የሚኖር ሞትንስ የማያይ ሰው ማን ነው? ነፍሱንስ ከሲኦል እጅ የሚያድናት ማን ነው?” (መዝ.፹፰፥፵፰) በማለት እንደገለጸው ሞትን አሸንፎ የሚቀር ከሲኦልም መዳን የሚችል አልነበረም፡፡
✅በሐዲስ ኪዳን ግን ለኃጥኣን ነው እንጂ ለጻድቃን ሞት የገነት መውረሻ ነው፡፡ ኢትዮጳያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ “ሞቶሙሰ ለጻድቃን ሕይወቶሙ ውእቱ እስመ ለጻድቅ ይትሌዓል ቀርኑ በክብር ጻድቃን እለ አስመርዎ ለእግዚኦሙ ምድረ ብርህተ ወጽእዱተ ይወርሱ፤ የጻድቃን ሞታቸው ሕይወታቸው ነው፡፡ የጻድቅ ክብሩ እጅግ ከፍ ከፍ ይላልና፡፡ ጌታቸውን ደስ ያሰኙት ጻድቃን ብርህት ጽእዱት የሆነች ምድርን የወርሳሉ፡፡” በማለት ድጓ በተባለ ድርሰቱ ያስረዳል፡፡ ስለዚህ ለጻድቃን ሞተ ሥጋ ማለትም የነፍስ ከሥጋ መለየት ሕይወታቸው ነው፡፡ የነፍስ ሞት የለባቸውም፡፡ የነፍስ ሞት ካለባቸው ጥንቱኑ ጻድቃን ሊባሉም አይችሉም፡፡
✅ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም «ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር፤ የጻድቅ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው» (መዝ.፻፲፭፥፭) በማለት ስለሕዝቅያስ በተናገረው ኃይለ ቃል ያስረዳን የነፍስ ከሥጋ መለየት ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም፣ ውጣ ውረድ፣ ድካም ካለበት ዓለም ውጣ ውረድ ድካም ወደሌለበት ዓለም መሄድ እንደሆነ ነው። ስለዚህ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ በዚህች ዕለት የቅዱሳን ዕረፍት ነው እየተባለ ይነገራል። ድካም ካለበት ድካም ወደሌለበት ስለሆነ ዐረፈ ወይም ዐረፈች እየተባለ ይነገራል።
ለ. ኃጢአት፡- በኃጢአት ምክንያት የሚመጣ ሞትን እግዚአብሔር አልፈጠረውም፡፡ መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን እንደሚነግረን እንዲህ ያለው ሞት የሰው ልጅ የፈጣሪውን ትእዛዝ በመተላለፉ ምክንያት የሰለጠነበት ነው። «በሕይወታችሁ ስሕተት ለሞት አትቅኑ፤ በእጃችሁም ሥራ ጥፋትን አታምጡ። እግዚአብሔር ሞትን አልፈጠረምና፤ የሕያዋንም ጥፋት ደስ አያሰኘውምና። ነዋሪ ይሆን ዘንድ ፍጥረቱን ፈጥሮአልና፣ የዓለም መፈጠርም ለድኅነት ነውና፣ በእነርሱም ዘንድ የጥፋት መርዝ አልነበረምና፣ ለሲኦልም በምድር ላይ ግዛት አልነበረውምና። ጽድቅ አትሞትምና። ክፉዎች ግን በእጃቸውና በቃላቸው ጠሩት ባልንጀራም አስመሰሉት። በእርሱም ጠፉ። የእርሱ ወገን መሆን ይገባቸዋልና ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረጉ» (ጥበ.፩፥፲፪-፲፯) በማለት ነግሮናል።
✅ሕይወት የተባለው የጻድቃን ሞት እንጂ የኃጥአን ሞት አይደለም። ምክንያቱም ኃጥአን ምንም እንኳ ወደማያልፈው ዓለም የሚሄዱ ቢሆንም መከራ ወደ አለበት፣ ሥቃይ ወደሚበዛበት እንጂ ዕረፍት ወደአለበት መሄድ አይችሉም። መከራና ሥቃይ ወደሚበዛበት ዓለም መሄድ ደግሞ ሕይወት ሊባል አይችልም። እንዲያውም ነቢዩ ዳዊት «ሞቱ ለኃጥእ ጸዋግ፤ የኃጥእ ሰው ሞት ክፉ ነው» (መዝ.፴፫፥፳፩) በማለት አስረድቷል። ጻድቃን ግን ሞተ ሥጋን እንጂ ሞተ ነፍስን አያዩም። ኃጥኣን ደግሞ ሞተ ሥጋም ሞተ ነፍስም ያገኛቸዋል። ስለዚህ ለኃጥእ ሰው ሞተ ሥጋውም ሆነ ሞተ ነፍሱ ክፉ እንጂ መልካም የሚባል አይደለም።
✅ከላይም እንደገለጽነው ኢትዮጵያዊው “ሊቅ ኢትፍርሕዎ ለሞት ፍርህዋ ለኃጢአት፣ እስመ ሞትሰ ኢየኃድገክሙ ዘበላዕሉ ኃልዩ ወአኮ ዘበምድ፤ ሞትን አትፍሩ ኃጢአትን ፍሩ ሞት ግን አይተዋችሁምና ስለ ሰማያዊው አስቡ” በማለት የነገረን ከኃጢአት መራቅ ይቻላል፡፡ ከሥጋዊ ሞት ግን መራቅ አይቻልም፡፡ በእርግጥ ከድንገተተኛ ሞት ንስሓ ሳይገቡ ከሚመጣ ሞት፣ መዳን ይቻላል፡፡ ሰብአ ትካት በንፍር ውኃ ሲጠፉ ኖኅ ከነቤተ ሰቡ ድኗል (ዘፍ.፯፥፩-ፍጻሜ)፤ የሰዶምና የገሞራ ሕዝብ ሲጠፉ ሎጥ ከሁለት ልጆቹ ጋር ድኗል (ዘፍ.፲፱፥፲፪-፳፪) ፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ሥጋዊ ሞት ጊዜው ሊረዝም ይችላል እንጂ አይቀርም፤ የነፍስ ሞት ግን ማለት ከኃጢአት መራቅ ይቻላል፡፡ በሚቻል ነገር እንጂ በማይቻል ገር መታገል ደግሞ አግባብ ስላልሆነ መፈራት ያለበትን ብቻ ፍሩት በማለት ሊቁ ያስረዳናል፡፡
✅በዚህ ንኡስ ርእስ መግለጽ የተፈለገው ድንገተኛና አሰቃቂ በሆነ የሞት ቅጣት የተቀጡትንና የመቀጣታቸው ምክንያት ምን ነበር የሚለውን ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈውን ሁሉ መዘርዘር አይቻልም። ለምሳሌ ያህል የተወሰኑ ማሳያዎችን ብቻ እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡
ሀ. ሰብአ ትካት፡- እግዚአብሔር አምላካችን ከሰዎች ኃጢአት የተነሣ እጅግ አዝኖ የነበረበት ዘመን ነው፡፡ ከኃጢአታቸው ክፋትና ጽናት የተነሣም እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በመፍጠሩ ተጸጸተ የተባለበት ዘመን እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ በዚህም የከፋና እጅግ የጠነከረ ኃጢአታቸው በንፍር ውኃ ጠፍተዋል፡፡ በእነርሱ ኃጢአት ያልተጨመረው ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ትእዛዝ በአዘጋጀው መርከብ ድኗል፡፡ (ዘፍ.፯፥፩-ፍጻሜ)
ለ. ግብጻውያን፡- በግብጻውያን የተቃጣው አንዱ ሞት ነበር፡፡በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ እንደምናነበው እስራኤላውያን በፈርዖናውያን ዘንድ እጅግ የከፋ በደል ደረሰባቸው፡፡ እግዚአብሔርም “መከራቸውን አየሁ ለቅሷቸውንም ሰማሁ እንግዲህ ላድናቸው ወረድሁ” (ዘጸ.፫፥፱) በማለት ምክንያተ ድኅነት ይሆናቸው ዘንድ ሙሴን አስነሣ፡፡ በሙሴ መሪነት በእርሱ አምላካዊ ቸርነት እስራኤልን ከፈርዖናውያን ሊያድን ፈቃዱ በሆነ ጊዜና ፈርዖርናውያን ደግሞ እስራኤልን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባልሆኑ ጊዜ በዘጠኝ መቅሰፍት በዐሥረኛ ሞተ በኵር በዐሥራ አንደኛ ስጥመት ቀጥቶ እስራኤልን ነጻ አድርጓቸዋል፡፡ (ዘጸ.፲፩፥፩-፲)
ሐ. እስራኤላውያን፡- ከፈርዖናውያን ዘንድ በብዙ ተአምር ያወጣቸውን አምላክ ረስተው ጣዖት ማምለክ ጀመሩ፤ ባሕር ከፍሎ ጠላት ገድሎ ያሻገራቸውን፣ ደመና ጋርዶ በበረሃ የመራቸውን፣ መና አውርዶ የመገባቸውን፣ ዓለት ሰንጥቆ ውኃ አፍልቆ ያጠጣቸውን አምላክ ረሱና አሮንን “አሮን አሮን ግበር ለነ አማልክተ እለ ይቀውሙ ቅድሜነ ወእለ ይመውዑ ጸረነ ዝስኩሰ ሙሴ ዘአውጽአነ እምድረ ግብጽ ኢነአምር ከመምንተ ኮነ፤ አሮን አሮን ከፊታችን የሚቆሙ ጠላታችንን ድል የሚያደርጉ አማልክትን ሥራልን፤ ከግብፅ ያወጣን ሙሴ ምን እንደሆነ አናውቅም” ብለው ጥያቄ አቀረቡ፡፡ በአቀረቡት ጥያቄ መሠረት ወርቃቸውን ብራቸውን ጌጣቸውን ሁሉ ሰብብስቦ ቢያቃጥለው የተድቦለቦለ ነገር ወጣ ቅርጽ ሠርቶ አምላካችሁ ይህ ነው አላቸው፡፡ በብዙ ተአምር ከጠላት ያዳናቸውን አምላክ በተቀረጸ ምስል ለውጠው ማምለክ ጀመሩ (ዘጸ.፴፪፥፩-፳፱) ፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ተቆጣ በአንድ ቀን ሦስት ሺህ እስራኤላውያን ሞቱ፡፡
መ. ዳዊት፡- ዳዊት በበደለ ጊዜ ለቅጣት ከቀረቡለት ቸነፈር፣ ጦርነት፣ ረኃብ መካከል አንዱ ምርጫው ቸነፈር ነበር፡፡ የሦስት ዓመት ረኃብ በሀገርህ ላይ ይምጣብህን ፣ ወይስ ጠላቶችህ እያሳደዱህ ሦስት ወር ከእነርሱ ትሸሽን ወይስ የሦስት ቀን ቸነፈር በሀገርህ ላይ ይሁን በማለት ከታዘዙበት የእግዚአብሔር የቁጣው መገለጫዎች መካከል አንዱ ቸነፈርና በቸነፈሩ ምክንያት የሚመጣ ሞት ነበር፡፡ ዳዊት የእግዚአብሔር የቁጣው መገለጫ የሆኑትን ሦስት ትእዛዛት መርምሮ የመረጠው እግዚአብሔር መሐሪ ነውና ይምረናል በማለት ቸነፈርን ነበር፡፡ በእግዚአብሔር እጅ ብወድቅ ይሻለኛል ብሎ ቸነፈርን መርጦም ሰባ ሺህ ሰው ሞተበት (፪ሳሙ.፳፬፥፩-ፍጻሜ)፡፡
✅ከላይ የተዘረዘሩትን ምሳሌዎች መሠረት በማድረግ በአሁኑ ወቅት ዓለምን ስጋት ውስጥ የጣለው የኮቪድ-፲፱ (ኮሮና ቫይረስ) የዓለም ሕዝብ ኃጢአት እጅግ ከፍቶና እግዚአብሔርን አሳዝኖ የመጣ ሊሆን ይችላል ብሎት ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ በኃጢአታቸው ምክንያት በሞት የተቀጡ እንደነበሩ ሁሉ በደዌ የተቀጡም ነበሩ። ለምሳሌ፡-
✅ዖዝያን፡- ዖዝያን በንግሥናው ዘመን እግዚአብሔር እየረዳው ጠላቶቹን ድል እያደረገ በሰላም ይኖር ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኘው አገልግሎቱ ከመኖር ይልቅ የማይገባውን ነገር አሰበ፡፡ ልብሰ ተክህኖውን ለብሶ በቤተ መቅደሱ ሊያጥን ገባ፡፡ ሕዝቡና ካህናቱ ለአንተ ክብር አይሆንህም እያሉት በድፍረት ገባ በግንባሩ ላይ ለምጽ ወጣበት፡፡ ያልተሰጠውን ክህነት ሲሻ የተሰጠውን ንግሥና አጣ፡፡ በኃጢአቱ ምክንያት በለምጽ ተመታ፡፡ ለምጽ ስለወጣበት ሲሞት እንኳን የነገሥታቱ መቃብር ባልሆነ እርሻ ውስጥ ቀበሩት፡፡ (፪ዜና መዋ.፳፮፥፲፮-፳፫) እንግዲህ በብሉይ ኪዳን ዘመን ኃጢአት የመቃብር ቦታ እስከመከልከል ድረስ ያደርስ ነበር፡፡ ዛሬም ይህ ለዓለም ሕዝብ አስጊ የሆነው በሽታ የመጣው በኃጢአታችን ምክንያት ሊሆን ይችላል ብሎ በማሰብ መቅሰፍቱን ይመልስልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ይግድ ይላል፡፡
✅በዚህ ወቅት ሕግ ተላልፎ ለእርሱ ያልተፈቀደውን የክህነት አገልግሎት እፈጽማለሁ ብሎ ወደ ቤተ መቅደስ የገባው ዖዝያን ብቻ ሳይሆን ይህን ስሕተት መገሠጽ ሲገባው ፈርቶ ዝም በማለቱ ነቢዩ ኢሳይያስም በለምጽ ተመትቷል፡፡ (ኢሳ. ፮፥፮-፯) ዛሬ እንኳንስ ኃጢአት እየተሠራ ነው ብለን ባለመናገራችን በሠራነው ኃጢአት ብቻ እንኳን መቅሰፍት ቢመጣብን ምን እንሆን ይሆን ብሎ ማሰብ ተበጊ ነው፡፡
✅ከላይም እንደተገለጸው ሥጋዊ ሞት ከሆነ አይቀርም፡፡ ይህ ማለት ሰው በሃይማኖት ጸንቶ ቢኖር በበጎ ምግባር ፈጣሪውን ቢያስደስተው ከሥጋ ሞት አያመልጥም፡፡ ነገር ግን ከላይ እንደ ዘረዘርናቸውና እንደነዚህ ካሉት ድንገተኛ ሞቶች ይድናል፤ የንስሓ እድሜ ይኖረዋል፤ በፍጹም ግን ሳይሞት የሚኖር የለም፡፡ ስለዚህ ሥጋዊ ሞት እርሱም “ሞትስ አይተዋችሁምና” ብሎ እንደነገረን የማይቀር ስለሆነ መንፈሳዊውን ሞት ደግሞ ማምለጥ ስለሚቻል አትፍሩት ተባለ፡፡ ባጭሩ መፍትሔ ስላለው ነው፡፡++++++++ ።
06/03/2026
🔴➻➻➻➻🔵 🔵➻➻➻➻🔴
🔴«አብርሃም አቡክሙ ተመነየ ከመ ይርአይ ዕለትየ ወርእየሂ ወተፈሥሐ — አባታችሁ አብርሃም የእኔን ቀን ያይ ዘንድ ተመኘ፤ አይቶም ደስ አለው›› ዮሐ ፰፥፶፮ አንዴ አይሁድ የክርስቶስን አምላክነት ተጠራጥረው ወደጌታችን ቀረቡና እንዲህ አሉት: ‹‹በውኑ ከሞተው ከአባታችን አብርሃም ትበልጣለህን? ነቢያትም ሞቱ፤ ራስህን ማን ታደርጋለህ?›› ጌታችን ኢየሱስ ግን «አብርሃም አቡክሙ ተመነየ ከመ ይርአይ ዕለትየ ወርእየሂ ወተፈሥሐ — አባታችሁ አብርሃም የእኔን ቀን ያይ ዘንድ ተመኘ፤ አይቶም ደስ አለው›› አላቸው፡፡ አይሁድም «አንተ ገና ሃምሳ ዓመት ያልሞላህ እንዴት አብርሃምን አየህ?» ብለው ጠየቁት፤ እርሱም ቅድመ ዓለም በነበረው ዘመን የማይቆጠርለትን ድኅረ ዓለም ከድንግል ማርያም የተወለደው ልደት ዘመን የሚቆጠርለት ቢሆንም ቀዳማዊ ልደቱን ያልተረዱ አይሁድ ጌታችንን እንዲህ ባሉት ጊዜ ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አብርሃም ሳይለወድ እኔ አለሁ›› አላቸው፡፡ ከዚያም ሊደበድቡት ድንጋይ አነሡ፤ ጌታችን ኢየሱስም ተሰወራቸው፡፡ (ዮሐ. ፰፥፶፮-፶፱)
🔵አባታችን አብርሃም የእግዚአብሔርን ቀን ለማየት ተመኝቶ አልቀረም፤ አይቶም ሐሴት አድርጓል፤ ይህም ደስታ ሥጋዊ ማለትም በልተው ጠጥተው እና ለብሰው የሚያገኙት ሳይሆን መንፈሳዊ ሐሴት ነው፡፡ ካልቀመሱት እና ካልደረሱበት በስተቀር የማይታወቅም ነው፡፡ ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ ፲፫ ላይ ተጽፎ እንደምናገኛው ቅዱስ አብርሃም ወንድሙ ሎጥን ተለይቶ በከነዓን በሚኖርበት ጊዜ አምስቱ ነገሥተ ኮሎዶጎሞር ሰዶምና ገሞራ ደርሰው ሎጥን ከነቤተሰቦቹ፣ ሀብትና ንብረቱ እንደማረኩት አብርሃም ሰማ፡፡
🔴አብርሃምም ፫፲፰ ቤተሰቦቹን ይዞ ሎጥ ተማሮኮበት ወደ ነበረው ፈጥኖ በመድረስ አምስቱ ኮሎዶጎሞርን ድል ነሥቶ ሎጥን ወደ ቀደመ ርስቱ መለሰው፡፡ ከተማረኩትም ውስጥ ብዙዎችን ስለ መለሳቸው እና ብዙ ምርኮ ስላገኘ ደስ እያለው ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡ ‹‹አብርሃምም የወንድሙ ልጅ ሎጥ እንደ ተማረከ በሰማ ጊዜ ወገኖቹንና ቤተሰቦቹን ሁሉ ቆጠራቸው፤ እነርሱም ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ሆኑ፤ እስከ ዳን ድረስ ተከትሎ አሳደዳቸው፡፡ እነርሱም ከብላቴኖቹ ጋር በሌሊት ደረሰባቸው፤ መታቸውም። በደማስቆ ግራ እስካለችውም እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው፡፡ የሰዶምን ፈረሶች ሁሉ አስመለሰ፤ ደግሞም የወንድሙን ልጅ ሎጥንና ንብረቱን ፥ሴቶችንና ሕዝቡንም አስመለሰ›› - ይላል (ዘፍ. ፲፬፥፲፬-፲፮)
🔵አባታችን አብርሃም እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት ሲወርድ አምላክን ከወለደች በድንጋሌ ሥጋ ድንጋሌ ነፍስ ከጸናች ከድንግል ማርያም ሰው ሲሆን ለማየት ስለ ተመኘ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ገልጦለታል፡፡አብርሃም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሊፈጽም ደስ ብሎት ዐሥራቱን፣ በኩራቱንና ቀዳምያቱን ይዞ ወደ አመለከተው ተራራ ሲደርስ ባሕታዊ መልከ ጸዴቅ ይኖርበት ከነበረው ዋሻ ወጥቶ ኅብስተ አኮቴት ጽዋ በረከት ይዞ ተቀበለው፤ መረቀውም፤ ‹‹አብርሃም ሆይ፥ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የእግዚአብሔር ክቡር ፍጥረቱ አንተ ነህ፤ ጠላቶችህንም በእጅህ የጣለልህ እግዚአብሔር ክቡር ምስጉን ነው›› አለው፡፡ አብርሃምም ዐሥራቱን በኩራቱን አቀረበለት፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር ወልድን ሰው መሆን አብርሃም አረጋገጠ፤ ዮርዳኖስን ተሻግሮ የመሄዱ ምሥጢር የጥምቀት ምሳሌ ነው ይላሉ አባቶቻችን፤ ዮርዳኖስ ወንዝን ተሻግሮ መልከ ጼዴቅን አግኝቶታል፡፡ መልከ ጼዴቅም የሰጠው ኅብስተ አኮቴት ጽዋዕ በረከት የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ምሳሌ ነው፡፡
🔴ነገር ግን ለአብርሃም መልከ ጸዴቅ ንጽሕናውን ከጠበቀለት በኋላ ነበረ ኅብስተ አኮቴት ጽዋዕ በረከት የሰጠው፡፡ እኛም ተጠምቀን ሥጋው ደሙን እንቀበላለን፤ በኋላም በምግባር ያሳደፍነውን በንስሓ ታጥበን ሥጋ ወደሙን እንድንቀበል ማሳያ በመሆኑ ነው፡፡ አብርሃምም የቅዱስ ቁርባን ምሥጢር ተገልጦለታልና ደስ አለው፡፡ (ዘፍጥረት አንድምታ ምዕራፍ ፲፬)
🔵የአብርሃም ጸጋ ይህ ብቻ አልነበረም፤ ከመንፈሳዊ ትጋቱ በተጨማሪ አላፊ አግዳሚውን እንግዳ እየተቀበለ ሲኖር ወደ አብርሃም ቤት እንግዶች እንዳይሄዱ እውነትን በሐሰት እየለወጠ ራሱን በድንጋይ የተመታ እያስመሰለ በአራቱም ማእዘን እየተገኘ ‹‹ወደ አብርሃም ቤት አትሂዱ፤ እርሱ አኮ የወትሮ አብርሃም አይደለም፤ እኔ ያበላኛል፤ ያጠጣኛል፤ አርፋለሁ ብዬ ብሄድ ራሴን በድንጋይ ገምሶኝ ከራሴ የሚወርደውን ደም ተመልከቱ፡፡ እንደ እኔ እንዳትሆኑ አትሂዱ›› እያለ ወደ ቤቱ እንግዳ ከለከለበት፡፡ አብርሃም ደግሞ ያለ ምስክር እንዴት ማዕድ ይቆረሳል ብሎ ሳይበላና ሳይጠጣ ሦስት ቀን ሰነበተ፡፡ በሦስተኛ ቀንም የእርሱን ደግነት የሰይጣንን ክፋት የተመለከተ ልዑል እግዚአብሔር ወደ አብርሃም ቤት አንድነት በሦስትነት መጣ፡፡
🔴አብርሃምም ዓይኖቹን አንስቶ ሲመለከት ሦስት አረጋዊያንን አየ፤ ሮጦ ሄዶም ተቀበላቸው፡፡ ‹‹ውኃ እናምጣላችሁ፤ እግራችሁን እንጠባችሁ፡፡ከዛፉም ሥር ዕረፉ እንጀራም እናምጣላችሁና ብሉ፤ ከዚያም በባሪያችሁ ዘንድ አርፋችሁ በኋላ፥ወደ አሰባችሁት ትሄዳላችሁ አላቸው፡፡ ምኞቱም ሁሉ ተሳካለት፤ እግዚአብሔርም አንድነቱንና ሦስትነቱን ገለጠለት‹‹እንደምታየን ሽማግሌዎች ነን፤ የመጣነው ደግሞ ከሩቅ ነው፡፡ ስለዚህ አዝለህ ወደ ድንኳንህ አስገባን›› አሉት፡፡ አንደኛውን አዝሎ ወደ ድንኳን ሲያስገባ ሁለቱ በግብር አምላካዊ ገብተው ተገኙ፡፡ አብርሃምም ነገሩ እየረቀቀበት ሲሄድ በጓዳ ለነበረችው ለሚስቱ ሣራ ‹‹ሦስት መስፈሪያ የተሰለቀ ዱቄት ፈጥነሽ ለውሺ፤እንጎቻም አድርጊ አላት፡፡ አብርሃምም ለሚስቱ ይህንን ያለበት ምክንያት ምሥጢረ ሥላሴን ስለተረዳ ነበር፡፡ ሦስቱ መስፈሪያ የሦስተነታቸው ምሳሌ ሲሆን አንዱ እንጎቻም ተዳርጎ መጋገሩም ደግሞ አንድነታቸውን ይገልጻል፡፡
🔵ሚስቱም እንዳዘዛት አድርጋ ጋግራ አቀረበች፤ እርሱም ቤት ለነበረ አንድ ብላቴና ወይፈኑን አርዶ አወራርዶ እንደያመጣለት ካዘዘው በኋላ ከወተትና ማር ጋር አብሮ አቀረበላቸው፡፡ እነርሱም አብርሃምን ደስ ለማሰኘት በሉ፤ ከዚያም የታረደው እና የተወራረደው ወይንም ተነሥቶ በድንኳኑ ደጃፍ ‹‹ስብሐት ለአብ፣ ስብሐት ለወልድ፣ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ›› ብሎ ሥላሴን አመሰገነ፡፡ አብርሃም ደነገጠ፤ ‹‹እንግዳ ከመጣልህ በትሑት ሰብእና በቅን ልቡና ሆነህ ተቀበል፤ እንግዳ ካልመጣ ጾምህን አትደር›› አሉት፤ ከዚያም ይስሐቅ የሚባል ልጅ እንደሚወልድ ነገሩት፡፡ (ዘፍጥረት አንድምታ ምዕራፍ ፲፰)
🔴ሥሉስ ቅዱስ በአብርሃም ድንኳን በመገኘታቸው በእርጅና የነበረ የሣራ ማሕፀን ተፈታ፤ ከሦስቱ አንዱም ‹‹የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ወደ አንተ ተመልሼ እመጣለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች›› አለ፡፡ ሣራ ግን በድንኳኑ ደጃፍ በስተኋላው ሆና ይህን ስትሰማ ‹‹እስከ ዛሬ ገና ነኝን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሏል›› ብላ በልቧ ሳቀች፡፡ አእምሮ ያረቀቀውን፣ ልቡና ያመላለሰውን የሚያውቅ ፈጣሪ ‹‹ሣራን ለብቻዋ በልብዋ ምን አሳቃት፤ “እስከ ዛሬ ገና ነኝን? በእውነትስ እወልዳለሁን? ጌታዬም አርጅትዋል፤ እነሆ እኔንም አርጅቻለሁ” ብላለች፤ በእውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ልጅን ታገኛለች›› አለ፡፡ ሣራም ስለ ፈራች “አልሳቅሁም” አለች፤ እርሱም “አይደለም፤ ሳቅሽ እንጂ” አላት›› በዚህም ልጇን ይስሐቅ ብላ ጠራችው፡፡
🔵 አብርሃምም ጎዶሎው ሞላለት፤ ጻድቁ አባታችን ሥላሴን ሲያስተናግድ በድንኳኑ ውስጥ ምንም ዓይነት ደባል ነገር አልነበረም፡አምላኩ እግዚአብሔርም ብቻ ነበር፤ ‹‹እኔና ቤት ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን›› እንዲል (ዘፍ. ፲፰፥፲፭፣ ኢያ. ፳፬፥፲፭) አብርሃም ዘረኛ አልነበረም፤ እንግዳ ተቀብሎ ያበላው ያጠጣውም ያገኘውን ሰው ሁሉ እንጂ ቋንቋ ወይንም ዘር እየጠየቀ አልበረም፡፡ በዚህም እግዚአብሔርን በአንድነትና በሦስትነት በቤቱ ለማስተናገድ በቅቷል፡፡
🔵የአብርሃም ድንኳን የእመቤታችን ምሳሌ ናት፤ አብርሃምም በሥላሴ ፊት ሞገስ በማግኘቱ ሥሉስ ቅዱስን እንዳስተናገደ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን ተልኮ የነገራት ይህንን ነበር፤ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት ባለሟልነትን አግኝተሻል›› ብሎ የሥላሴ ማደሪያ እንድትሆን መመረጧን አብሥሯታል፡፡ የአብ ሙሽራ፣ የወልድ እናት፣ የመንፈስ ቅዱስ ንጽሕት አዳራሽ የምታባለውም ለዚህ ነው፡፡ (ሉቃ. ፩፥፴)
🔴ቅዱስ አብርሃም ይህ ምሥጢር የተገለጠለት ከብዙ ፈተና በኋላ ነበር፤ ሕይወቱን በሙሉም በፈተና ኖሯል፤ ተርቧል፤ ተጠምቷል፤ ተሰድዷልም፤ እግዚአብሔር የሚገለጥለት ጻድቅ ሰው ሆኖ እንኳን አብርሃም በሥጋው ይፈተን ነበር፡፡ እግዚአብሔርንም ለሦስተኛ ጊዜ ያየው ልጁ ይስሐቅን ከወለደ በኋላ ነበር፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን ዳግም ፈተነው፤ ‹‹የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ከፍተኛው ተራራ ሂድ፤ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው›› አለው፤ በስተርጅና የተወለደ ልጅ ቢያሳሳም አብርሃም ግን ለእግዚአብሔር ሊሰጠው አልሳሳም፡፡ እንደሰማም ይዋል ይደር ሚስቱንም ላማክራት አላለም፤ ‹‹ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ፈጽሞ አበዛዋለው፤ ዘርህም የጠላት ሀገሮችን ይወርሳሉ፤ የምድር አሕዛብ በዘርህ ይባረካሉ›› ብሎ የገባለት ቃል ኪዳን በይስሐቅ በኩል እንደሚፈጸም ቢያውቅም አልተጠራጠረም፡፡ (ዘፍ.፳፪፥፪ ፣ ፲፯-፲፰)
🔴ስለዚህም አብርሃም ልጁ ይስሐቅን ይዞ ሁለት ሎሌዎቹን አስከትሎ ሦስት ቀንና ሌሊት ከተጓዘ በኋላ እግዚአብሔር ከአዘዘው ተራራ ደረሱ፤ ከእግረ ደብሩም ሎሌዎቹን ትቶ ይስሐቅን እንጨቱን እንዲሸከም ካደረገ በኋላ ሸተሉን እና እሳቱን በእጁ ይዞ ሎሌዎቹን ‹‹እኔና ልጄ ወደዚያ ተራራ ሄደን እንሰግዳለን፤ ሰግደንም ወደ እናንተ እንመለሳለን›› አላቸው፡፡ ተነሥተውም ሲጓዙ ይስሐቅ ‹‹አባቴ ሆይ፥ አለ፤ እርሱም፥ ልጄ፥ ምንድን ነው? አለው፤ እሳቱና ዕንጨቱ ይኸው አለ፤ የመሥዋዕቱ በግ ግን ወዴት አለ?›› አለው፡፡
🔵አብርሃምም ልጁን ‹‹ልጄ ሆይ፥ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል›› ብሎ መለሰለት፡፡ ከተራራውም ሲደርሱ መሠዊያውን ሠራ፤ ዕንጨቱንም ረበረበ፤ ልጁ ይስሐቅም እርሱ መሥዋዕቱ እንደሆነ ዐወቀ፤ ‹‹አባቴ ስወራጭ እጅህን እንዳላስቆርጥህ እሰረኝ›› አለው፤ አብርሃምም ልጁን አስሮ በመሠዊያው በዕንጨቱ ላይ በጀርባው ሲያስተኛው ‹‹የልጅ ዓይኑ ብክን ብክን ሲል ያሳዝናልና እራርተህና አዝነህ ትተኸኝ ከፈጣሪህ ጋራ እንዳትጣላ ደረቴ አስተኛኝ›› አለው፤ አብርሃምም ልጁን በልቡ አስተኛው፤ እጁን ዘርግቶም ልጁን ያርድ ዘንድ ቢላዋ አነሣቶ አንገቱ ላይ ሊያሳርፍ ሲል እግዚአብሔር አብርሃምን ጠራው፤ ‹‹አብርሃም! አብርሃም አለው፤ እርሱም እነሆኝ አለ፤ በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፤ አንዳችም አታድርግብት፤ ለምትወደው ልጅህ ከእኔ አልራራህለትምና አንተ እግዚአብሔር የምትፈራ እንደሆንህ አሁን ዐውቄአለሁ›› አለው፡፡ (ዘፍጥረት አንድምታ ምዕራፍ ፳፪)
🔴አብርሃምም ዓይኖቹን ቀና አድርጎ ሲመለከት ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ የተያዘ በግ ለአብርሃም ወረደለት፤ ያንን በግም በልጁ ፈንታ ሠውቶ ደስ እያለው ተመለሰ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ሲል የመሠዋቱን ምሥጢር ተመልክቷል፤ ይስሐቅም የክርስቶስ ምሳሌ ነውና፡፡ ልጁን በሦስተኛው ቀን በሕይወት አግኝቶታል፤ የባሕርይ አምላክ ክርስቶስም በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ ወደ በመቃብር ወርዶ በሦስተኛው ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል የተነሣ መሆኑን ያመለክታልና ይህን ምሥጢር እግዚአብሔር አምላክ ለአብርሃም ገለጠለት፡፡
🔵ዕፀ ሳቤቅ እመቤታችን ምሳሌ ናት፤ ቅጠል የበዛበት ሐረግ በመሆኑ የድንግል ማርያም ምስጋናዋ የበዛ ንጽሕናዋና ቅድስናዋ የተለየ ከነገደ መላእክት በክብር የሚመስላት በጸጋ የሚተካከላት እንደሌለ አመላካች ነው፡፡ በዚህም የእመቤታችንን ክብር ገልጾለታል፡፡ የበጉ ከሰማይ መውረድም የጌታችንን ከሰማይ መውረድ የሚያመለከት ነው፤ አብርሃም የሰዋው አንድ በግ ነው፤ ይህም የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ አንድ ልጁን የመሠዋቱ ምሳሌ ነው፤ ስለዚህ አባታችን አብርሃም ይህንን ምሥጢር ለማወቅ ከነቢያት ይቀድማል፡፡ ምክንያቱን ምሥጢሩን ነቢያት በትንቢታቸው የገለጹት ለሕዝቡም በትምህርታቸው ያስታወቁት ከዚህ በኋላ ነው፡፡
🔴አባታችን አብርሃምም ይህንን ሁሉ ምሥጢር ተረድቶና ፈጣሪው እግዚአብሔርን ደስ አሰኝቶ እና አገልግሎ በክብር ዐረፈ፤ እኛንም እያማለደን በሰማይ ቤት ይኖራል፤ ‹‹በምድር የሠሩት በሰማይ ይከተላቸዋል›› እንደተባለው በዚህም ምድር የሠራውን ሥራ በሰማይ እየተገበረው ይገኛል፡፡ ሥራውም እንግዳ መቀበል ስለ ነበር ዛሬ እኛም ‹‹ከምድር የሚለየቱን ሁሉ በአብርሃም አቅፍ አሳርፍልን›› እያልን እንደምንለው አሁንም እንግዳ እየተቀበለ ይገኛል፡፡ (ራእ.፲፬፥፲፫) የአባታችን የአብርሃም በረከት ይደርብን፤ እኛም በሰማነው፣ ባየነውና በተረዳነው ሃይማኖታችንን፣ አጽንተን እና ቅዱሳንን መስለን እንድንኖር እግዚአብሔር ይርዳን፤ አሜን፡፡
06/03/2026
🔵➻➻➻📶 📶➻➻➻🔵
✅ወስርሑ እንዘ የኀሥሥዎ ለውእቱ ኆኅት:- ደጃፉንም ለማግኘት ሲፈልጉ ደከሙ /ዘፍ.19፥11 ለዚሁም በቸርነቱ ብዛት እውቀትን ጥበብን ምስጢርንና ማስተዋልን ለሰው ልጆች ሁሉ የሚገልጥ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የራቀውን አቅርቦ የረቀቀውን አጉልቶ የተሰወረውን ገልጦና የተከደነውን ከፍቶ የቅዱሳት መጻሕፍትን ጥልቅ ሃሳብ እንድንረዳ ይርዳን!ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር። ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ፥ አላቸውም፦ ጌቶቼ ሆይ፥ ወደ ባሪያችሁ ቤት አቅኑ፥ ከዚያም እደሩ፥ እግራችሁንም ታጠቡ ነገ ማልዳችሁም መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ አላቸው ።
✅እነርሱም፦ በአደባባዩ እናድራለን እንጂ፥ አይሆንም አሉት።እጅግም ዘበዘባቸው ወደ እርሱም አቀኑ፥ ወደ ቤቱም ገቡ ማዕድ አቀረበላቸው፥ ቂጣንም ጋገረ እነርሱም በሉ።ገናም ሳይተኙ የዚያች ከተማ የሰዶም ሰዎች፥ ከብላቴናው ጀምሮ እስከ ሽማግሌው ድረስ በየስፍራው ያለው ሕዝብ ሁሉ፥ ቤቱን ከበቡት። ሎጥንም ጠርተው እንዲህ አሉት፦ በዚህ ሌሊት ወደ ቤትህ የገቡት ሰዎች ወዴት ናቸው? እናውቃቸው ዘንድ ወደ እኛ አውጣቸው። ሎጥም ወደ እነርሱ ወደ ደጅ ወጣ መዝጊያውንም በኋላው ዘጋው እንዲህም አለ።
✅ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህን ክፉ ነገር አታድርጉ እነሆ፥ ወንድን ያላወቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ እነርሱን ላውጣላችሁ፥ እንደ ወደዳችሁም አድርጓቸው በእነዚህ ሰዎች ብቻ ምንም አታድርጉ፥ እነርሱ በጣራዬ ጥላ ሥር ገብተዋልና አላቸው እነርሱም፦ ወዲያ ሂድ አሉት።ደግሞም እንዲህ አሉ ይህ ሰው በእንግድነት ለመኖር መጣ፥ ፍርዱንም ይፈርድ ዘንድ ይፈልጋል -አሁን በአንተ ከእነርሱ ይልቅ ክፉ እናደርግብሃለን አሉት። ሎጥንም እጅግ ተጋፉት፥የደጁንም መዝጊያ ለመስበር ቀረቡ። ሁለቱም ሰዎች እጃቸውን ዘርግተው ሎጥን ወደ እነርሱ ዘንድ ወደ ቤት አገቡት መዝጊያውንም ዘጉት።በቤቱ ደጃፍ የነበሩትንም ሰዎች ከታናሻቸው ጀምሮ እስከ ታለቃቸው ድረስ አሳወሩአቸው ደጃፉንም ለማግኘት ሲፈልጉ ደከሙ።"(ዘፍ 19፥1-11)
📶 📶
✅ሎጥ ለታራን ልጆቹ የሚሆኑ "አብራም" እና ናኮር የተባሉ ሁለት አጎቶች የነበሩት የካራን ልጅ ነው:: አብርሃምን ተከትሎ ካራንን ጥሎ ከአምልኮ ባዕድ ተነጥሎ የወጣ ኋላም በሁለቱ እረኞች መኃል የተከሰተው ጸብ ወደ ርስት መከፋፈል ቢያመራ ሎጥ እንደ እግዚአብሔር ገነት በግብፅ ምድር አምሳል የሆነችውን ሰዶምን ሲመርጥ"አብራም" ግን በከነዓን ተቀመጠ"መጻተኛ ይኖር በአገር ይሰጡት ከድንበር" እንዲሉ አላስጠጉትም፡፡ ያም ቢሆን የሰዶም ሰዎች ኃጢአትን ሲያበዙ ሎጥ ከግብራቸው አልተባበራቸውምና በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር ይለናል፡፡
✅እንዲያውም ውድቀቱን እያየ በዓመጻ ሥራቸው አልተባበረም ነበር:: ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ እንዳለ "ኀጥኣን ሲበዙ ኃጢአት ትበዛለች፤ ጻድቃን ግን ውደቀታቸውን ያያሉ።"(ምሳ.29፥16) ይልቁንም ጽናቱን ለሁላችን አብነት እያደረገ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ የጻድቁን ኑሮ በሚከተለው መልኩ አስተምሮናል፡- "ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና(2ኛ.ጴጥ.2፥7-8) በቤቱም መላእክትን አስጠለለ፡፡ የቤቱም ደጃፍ በቅዱሳኑ ተጎብኝታለችና ኃጢአተኞች ሊቀርቧትና ሊዳፈሯት እንዳይቻላቸው አይናቸው ተያዘ። ኋላም በአገሪቱ ኃጢአት እርሱም ቤተሰቡም እንዳይጠፉ በቅዱሳን መላእክቱ እርዳታ ወደ ምስጋረ እግር "ሴጎር" ተሻገረ።
🦋 🦋
✅"የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጢአተኞች ነበሩ።"ይለናል ዘፍጥ 13 ፥13)፡፡ተመልከቱ ብጹዕ ሰው በክፉዎች ምክር ያልሄደና በኃጢአተኞች መንገድ ያልተቀመጠ ነው:: ክፉ ማለት ነፍሱን ያጎደለ ኃጢአተኛም አምላኩን የበደለ ነውና(መዝ.1፥1) ጻድቅ ሎጥ ግን በመካከላቸው ሲኖር በክፋትና በኃጢአት ሥራቸው ያልተባበረ ብጹእና ጻድቅ ሰው ነበር :ሰዶማዊነት :- ከእንሰሳዊነት በባሰ አጋንንታዊ ተግባርና እና አምላክን በእጅጉ ያሳዘነ በነዋሪዎቹ ስም የተጠራ ሕሱም ተግባርና የከበደ ኃጢአት የከፋ በደልም ነው።(ዘፍ18፥20) ለመሆኑ
✅ዓይነ ሥጋቸው ከማየት የፈዘዘውና ዓይነ ሕሊናቸው ከማስተዋል የደንነዘዘው ሰዶማውያን ወደዚህ ክፉ ሥራቸውና ሕግ መተላለፋቸው እንዲያመሩ ያስገደዳቸው ኃጢአት ምን ነበር? ነቢዩ ሕዝቅኤል ምክንያተ ሰዶማዊነትን እንዲህ እያለ ያስቀምጥልናል"የሰዶም ኃጢአት ይህ ነበረ፡ትዕቢት፣እንጀራን መጥገብ፣ መዝለልና ሥራ መፍታት" (ሕዝ.16፥49):: እስኪ እነዚህን ነጥቦች ለዓይን መታወርና ደጃፉን ለማጣት እንዴት እንደሚያደርሱ እንመልከት፡፡
1· #ትዕቢት፦እንቆጳዝዮን ሊቁ ልሳነወርቅ ዮሐንስ ትዕቢት የኃጢዓት ሥር ምንጭና እናት ናት እንዳለን በቅዱስ መጽሐፍም ውስጥ ጥበብና እግዚአብሔርን መፍራት ያላቸው ዝምድና ያህል ትዕቢትና ኃጢዓት እንዲሁ ናቸው ተመልከቱ "የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፥" "እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው" = "እግዚአብሔርን የመፍራት መጨረሻ ጥበብ ነው" (መዝ.110፥10, ምሳ1፥7, ኢዮ 28፥28, ሲራ 21፥11 ) በአንጻሩ ደግሞ:-"ትዕቢተኛ ዓይንና ደፋር ልብ የኀጥኣንም እርሻ ኃጢአት ነው።የኃጢአት አበጋዝዋ ትዕቢት ናት"(ምሳ.21፥4,ሲራ.10፥13) ፡ትሑታን ከፈጣሪያቸው መልካም ገጸ በረከትን በጎ ዕድልን ሲቀበሉ ትዕቢተኞች ግን ከአምላካችን ተቃውሞ ያገኛቸዋል::
✅በዚህም የከበሩ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ያዕቆብ እንዲህ እያሉ ተባብረውበታል፡"እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። ""ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል።"(1ኛ.ጴጥ. 5፥5, ያዕ. 4፥6)::እመ ትሕትና ብላቴናዋ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዓለሙን ሁሉ መድኅን በማህጸንዋ ተሸክማ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል "ወላዲቱ ለወልደ እግዚአብሔር" እያለ ሲያመሰግናት ቅድስት ኤልሳቤጥም "እሙ ለእግዚእየ" ብላ እያጸናችላት ራስዋን ግን እናቱ ሳይሆን አመቱ (ሴት ባርያው) እያለች ገለጸች፡፡ ተመልከቱ ለኛም የሚሻገረውን መልእክት በጸሎትዋ እንዲህ ብላ አስተማረችን "ወገብረ ኃይለ በመዝራእቱ ወዘረዎሙ ለእለ የአብዩ ህሊና ልቦሙ.በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤" ጸሎተ እግዝእትነ ማርያም (ሉቃ.1፥51)::እንግዲህ ልብ እናድርግ በጉልበቱና በሀብቱ በእውቀቱና በውበቱ የሚመካ ትዕቢተኛን ሰው ክፋትን ያደርጋልና አምላኩ በእጅጉ ያዝንበታል "አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንደዚህ ያለ ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው።"(ያዕ.4፥16)
1·1 ፦ፍጡር ኃጢአት ሲሠራ ምድራዊ ጊዜአዊ እና ሥጋዊ ዓይኑ ይከፈታል፡፡ በዚያው መጠን ሰማያዊ መንፈሳዊ ዘለዓለማዊ ዓይኑ እስኪታወር ይደክማል:: በተለይ ደግሞ ለዚህ እንደምሳሌ ፈጣሪውን አመስግኖ ክብሩን ለመውረስ የተፈጠረው ሳጥናኤል በትዕቢት ወድቆ ብርሃን የሆነ እውቀት ሲገለጥ ጨለማ በሆነ ድንቁርና የኖረው ተዋርዶ ሲጣልም "እግዚአብሔር ጎየ እግዚአብሔር ሸሸ" ያለው ስለታወረ ነው::
✅"አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥እንዴት ከሰማይ ወደቅህ አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቈረጥህ! አንተን በልብህ። ወደ ሰምይ ዐርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፥ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ: ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ።ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጕድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ።"(ኢሳ 14፥12-15)ውሳጣዊው መንፈሳዊ ዓይን ረቂቁን እንጂ ደረቁን ለማጤን የተፈጠረ አይደለም::ይህችን ዓይነ ሕሊና ብርሃነ ልቡና ትሕትናን ቀለብ አድርገውራሳቸውን ገዝተው የተጠቀሙባት ይከብሩባታል፤ ትዕቢተኞች ግን ይዋረዱባታል "የትዕቢተኞችም ዓይን ትዋረዳለች. አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፥ የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ።" (ኢሳ.5፥15, መዝ.18፥27)
1·2 ፦እንግዲህ ሁሉም ሰው የትዕቢትን ጨለማ የዓይኑን ቅርፊት የኃጢአት ሰንኮፍ ጳውሎስ እንደተባለ ሳውል በንሰሐ ካላነሣ ወደ ጥልቁ ጨለማ ወደ ዘለዓለም ድንቁርና ይጋዛል:: "ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ፤አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድኻም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥...እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ።"(ራእ. 3፥17) ስለዚህ ንሰሐ አጥርቶ ለማየት የሚያግዝ ኩል ለሁሉም የተሰጠ ፍኖተ ጽድቅ በተአምኖ ኃጣውዕ የሚኖሩበት የትሕትና ሥራ ነውና ሁላችን ነገን ለመክበር ዛሬ ሁሉን ከፍ ከሚያደርገው ጌታችን በታች ራሳችንን በትሕትና እናዋርድ፡፡ ሊቀ ሐዋርያት እንዲህ እንዳለ "እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤"1ኛ.ጴጥ.5፥6
2· #ጥጋብ፦ይህ ሁለተኛው የሰዶም ኃጢአት ነው:: ጥጋብ ማለት ይላል ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ "ሰው ቁሳዊ ምልአትን ሲሻ በሚያልፈው ላይ ትውክልቱን ሲያኖር ለመንፈሳዊ እሴቶቹ ትኩረት ሲነፍግ የሚታይ መገለጫ ነው::ሐዋርያው ለሁላችን በሚጠቅመን ምክሩ ይህን ብሎናል፡-ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥
አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል።" (1ጢሞ. 6፥6-8)
✅ ደጉ ሰው አባታችን ያዕቆብ የምጠግበውን ከማለት ይልቅ "የምበላውን እንጀራ" እያለ የለመነው (ዘፍ.28፥20) እኛም ጌታችን ባስተማረን ምስጋናና ልመና የምንጠይቀው እንዲህ እያልን ነው:-"ሀበነ ዮም ሲሳየነ ዘለለ ዕለትነ" (ማቴ 6፥11)፡፡ ምክንያቱም መብል በሥጋ ለመኖር እጅጉን ጠቃሚ የኑሮ መሠረትና የጉልበት ጽናት ነው፡፡"እክል ያጸንዕ ኃይለ ሰብዕ .እህልም የሰውን ጕልበት ያጠነክራል።"የኑሮህ መጀመርያ የምትበላው እህል ...ነው" (መዝ.103፥15, ሲራ 29፥21) እንዲል:: ነገር ግን ሁሉ በልክ ሊሆን ይገባልና ለቁመተ ሥጋ ጸንቶ ለማገልገል ኃይል የሚሆነውን ካገኙ የቀረውን ያን አጥቶ ለተቸገረው መመጽወት ይገባል::"አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፥ መከራን ተቀበል፥" ይላልና (2ኛ.ጢሞ.4፥5)
✅ነገር ሁሉ ከልክ ያለፈ ቢሆን ግን ከአምላክ ይለያል ጥጋብም ሰውን ከፈጣሪው ቤት ያባርረዋል፤ለሆዱ ያሳድረዋል:: እስራኤል ዘሥጋን ያገኛቸው ይህ ነው፡፡ "ከተሰማሩ በኋላ ጠገቡ፥በጠገቡም ጊዜ ልባቸው ታበየ ስለዚህ ረሱኝ።(ሆሴ.13፥6) ከዚህም ጋር አካተን አንድ ነገር እንመልከት፡፡ሰው ሲጠግብ እንኳን ለፈጣሪው ፈቃድ መገዛት ቀርቶ ራሱን መግዛት የማይቻለውና ስሜቱ የሚገዛው ለምኞቱ ተላልፎ የሚሰጥ ይሆናል፡፡"በሉ እጅግም ጠገቡ ምኞታቸውንም ሰጣቸው።"(መዝ.78፥29) እንግዲህ ሰው ሲጠግብ የማይረባውን ለማግኘት የሚምስ መልካሙን ወደማየት የማይመለስ ይሆናል፡፡ይህንንም መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን እንዲህ ሲል በቁሙ ያሳየናል "የጠገበች ነፍስ የማር ወላላ ትረግጣለች(ምሳ.27፥7)
✅ጥጋብን የሚከተል ቢኖር ነገን የሚያኖር እግዚአብሔር መሆኑን የዘነጋ የተቸገረ ወገኑን የማያስታውስና ደስታውን በጊዜአዊ ፈቃዱ ላይ የገነባ በመሆኑ አምላኩ ፈጽሞ የሚያዝንበት እስኪሞትም መተላለፉ የሚያዝበት ከንቱ ሰው ነው"እነሆም፥ ሐሜትና ደስታ በሬውንና በጉንም ማረድ ሥጋንም መብላት የወይን ጠጅንም መጠጣት ሆነዋል፡፡ እናንተ ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣ ብላችኋል።ይህም ነገር በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ጆሮ ተሰማ። እስክትሞቱ ድረስ ይህ በደል በእውነት አይሰረይላችሁም ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር" (ኢሳ. 22፥13-14)
2· "፦አምላኩን በትዕቢት ክዶ በወረደው ዲያቢሎስ ፈንታ የተፈጠረው የሰው ልጅ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ "ረቂቅ የምትሆን ከነፋስና ከእሳት የተፈጠርክ አንተ ፈጣሪ ነኝ በማለት በታበይክ ጊዜና አንተ በተመካህ ጊዜ ከሰራዊቶችህ ጋር እግዚአብሔርን ክደሃልና እግዚአብሔር ክፉ ሥራህን አይቶ ሳያጓድል ስሙን እንዲያመሰግን አዳምን ፈጠረ" (3መቃ.2፥10)፡፡ ይሁንና ግን ሰው ለሆዱ ማደሩ በጨመረ ቁጥር ሕሊናውን እየሸጠ ወደ መክሰር ተሻገረ:: በልማድ "ሆድ ሲሞላ ጭንቅላት ባዶ ይሆናል" እንደሚባለው:: አዳምና ሴቲቱ በምክረ ከይሲ ተረትተው የተፈጠሩበትን ክብር ገፍተው እጸ በለስን በልተው ሥጋዊ ዓይናቸው በተከፈተ ጊዜ መንፈሳዊ ዓይናቸው ታወረ::
✅"እባብም ለሴቲቱ አላት። ሞትን አትሞቱም ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።" "የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ" (ዘፍ 3፥4-5, ዘፍ.3፥7)ተመልከቱ! ጠላት ሰውን ሲጥል በምግብ ይፈትነዋል .ቀድሞ አዳምና ሔዋን በመብል የጣለው ፈታኝ ኋላ ለወንድሞቹ ስንቅ ለማድረስ የደከመ ዮሴፍን ሲርበው ተጠግቶ ብላባቸው አለው፡፡ ብላቴናው ግን አልተበገረለትም ያም አልበቃው ቢል ወደ ጌታችንም ቀርቦ ደንጊያውን ዳቦ ቢያደርግ እንደሚበሉ አወያየው፡፡ ክርስቶስ ግን ተርቦ ሳይሳሳ ተፈትኖ ድል ሳይነሳ አሳፈረው::ታዲያ ለሆዱ ያደረ ምን ተጠቀመ? ምንስ አተረፈ? የሆዱን ፈቃድ ገፍቶ የተወስ ምን ቀረበት ምንስ አጎደለ? "መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጎድለንም ብንበላም ምንም አይተርፈንም።"(1ኛ.ቆሮ.8፥8)
2· ፦በልክ የሚበላ የሥጋውን ምኞት ለመከልከል አቅም የማያጣ ለፈጣሪውም ፈቃድ ለማደር ጉልበት የማይከዳው ሰው ምንኛ ብርቱ ሰው ነው:: "እጅግ ወይም ጥቂት ቢበላ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው የባለጠጋ ጥጋብ ግን እንቅልፍን ይከለክለዋል።" ይለናል (መክ.5:12)፡፡ እስኪ ሁላችን ከጠቢቡ ንጉሥ ጋር ሆነን በጋራ ይህንን እንለምን ፡- "ሁለትን ነገር ከአንተ እሻለሁ፥ ሳልሞትም አትከልክለኝ: ከንቱነትንና ሐሰተኛነትን ከእኔ አርቃቸው፡፡ ድኅነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ፡፡ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ፥ እንዳልጠግብ እንዳልክድህም። እግዚአብሔርስ ማን ነው? እንዳልል ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም፥ በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል።" (ምሳ. 30:7-9)
3· ፦መዝለልና ሥራን መፍታት በአንድነት
ከትጋት ለመራቅ ለግድ-የለሽነት መገለጫዎች ናቸው።በ3ተኛ ነጥብነት አካተን እንመለከታቸዋለን:ይህም በንሰሐና መስቀሉን በመሸከም ከመኖር ይልቅ ወደ ጥፋት የሚወስደውን ሰፊ መንገድና የተቀማጠለውን ኑሮ የሚመርጡ ሰዎች መገለጫ ነው::እንደዚህ ያሉቱ ግድ የለሾች በመጽሐፍ እንዲህ ተቀምጠዋል "ከዚህም ጋር ቤት ለቤት እየዞሩ ሥራን መፍታት ደግሞ ይማራሉ፥
የማይገባውንም እየተናገሩ ለፍላፊዎችና በነገር ገቢዎች ይሆናሉ እንጂ፥ ሥራ ፈቶች ብቻ አይደሉም።"1ኛ.ጢሞ. 5፥13) ሰው ጥንቱን ከሥራ ጋር ለሥራ ነው የተፈጠረው፡፡ "እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው"እንዲል (ዘፍ.2፥15) ተግባር ከመፍታቱ የተነሣ የጠላት ቤተ ሙከራ የሆነ አእምሮ አዳዲስ ኃጢአቶችን ሲያቅድና ሲያመርት ይኖራል:: ለዚህም ነው ሰብአ ሰዶም በስማቸው የተጠራ ሰዶማዊነትን ያመረቱት። በሥጋ የደለቡ በነፍስ የተራቡ ሆነው ከሕገ ነፍስ ሕገ ሥጋ ከሕገ መላእክት ሕግ እንስሳ በልጦባቸው በገዛ በደላቸው ጠፉ። ተመልከቱ "ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው። (ምሳ. 12፥27,ምሳ.19፥15)
3· ፦ግድየለሽ የምንለው ሰው ሥራ ፈት፣ ፍሬቢስ፣ ትጋት አልባ ሆኖ በቅርብ ያለውን ምድራዊ ነገር ብቻ በሥጋ ዓይኑ የሚያይ በጥልቅ ያለውን ሰማያዊ ሀብት በመንፈሳዊ ዓይን የማይረዳውን "ዕውር" ነው! ስለዚህም ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን አስቀምጧል፡- "ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥ በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ። እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋልና፤ እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፥ የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቶአል።"(1ጴጥ.1፥5-9)
3. ፦የአልዓዛር ልጅ ሲራክ የተባለ ኢያሱ እንዲህ እያለ እስከ ዐረፍተ ዘመናችን እስከ ጊዜ ሞታችን እንድንተጋ ግድ-የለሽነትን እንድናርቅ ይመክረናል"በጊዜው ጊዜ ዋጋችሁን ይሰጣችሁ ዘንድ ይህ ዓለም የሚያልፍበት ጊዜ ሳይደርስ ሥራችሁን ሥሩ" ሲራ 51፥30፡፡
✅ #ማጠቃለያ፦ብዙዎች በትዕቢት በጥጋብና በግዴለችነት የታወሩ በደለኞች ደጃፎቿን ለማግኘት የደከሙባት ዓይነ ሕሊናቸው ከማስተዋል የደነዘዘ ዓይነ ሥጋቸው ከማየት የፈዘዘ ኃጥአን የከበቧት ይህች ደጅ "ደጀ ሰማይ" ቤተ ክርስቲያንና "ደጀ ሰላም" ድንግል ማርያም ናት:: ይህን ለማለት ለአንዳንዶች እንደሚመስላቸው በአመክንዮ አቀራርበን የምንጽፍ አልያም በሰው ጥበብ አመሳስለን የምንናገር አይደለም::
✅ይልቁንም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው መንፈሳውያን መጻሕፍትን የጻፉ ኄራን አበውን አብነት እናደርጋለን እንጂ "መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም።"(1ኛ.ቆሮ. 2፥13)በምሳሌነቱም በምስጢር የሚስማማውን የሎጥን ቤት ደጃፍ ብቻ አብነት እንወስዳለን እንጂ ስለ ሰዶም የተነገረ ሁሉ ለዚህ ፍቺ ሆኖ እንደማይገባ ልብ ይሏል:: እንደማሳያም ቅዱስ መጽሐፍ ሰዶምን የቀራንዮ ምሳሌ ያደርጋታል "በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ የተባለች ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት።"ራእ.11፥8 ይህም
✅የተመቸውን የአይሁድ አመጻ ሲያነጻጽር. በሌላም ሥፍራ የሰዶም እሳትና ዲን "እሳት በፊቱ ይነዳል" ለተባለ ንጉሥ የምጽአት ፍርዱ ምሳሌ ሆኖም ተቀምጧል "እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደ ሆነ፤ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ ሁሉንም አጠፋ።የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል። (ሉቃ.17፥28)ታዲያ የሰዶም እሳት ለፍርድ ቀን እሳት ምሳሌ ከሆነ እስከ ዓለም ማለፍ የቅዱሳን ምዕራፍ የጽድቅ ደጃፍ ቤተ ክርስቲያንና ድንግል ማርያምን እኛም ደጅ ብለን በዚህ ክፍለ ትምህርት አነሣን።
✅ ( )እንደ ሎጥ ያለ ጻድቅ የሚጠለልባትና ለቤቱ ንጽህና ራሱን አሳልፎ የሚሰጥባት እንደ መላእክትም ያሉ ቅዱሳን የሚጠብቋት ስብሐተ እግዚአብሔርን የሚመገቡባት መሥዋዕቱን የሚያሳርጉባት መነሻዋ ዓለመ መላእክት ቢሆን ለሰው ፍጥረት መጠለያነት በምድርም የጸናች ሥሯ በምድር ላይ ቅርንጫፎቿ በሰማይ የተባለች ኆኅተ ሰማይ የሰማይ ደጅ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ናት፡፡
✅ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ከቤራቤህ ወደ ካራን ሲሄድ ደንጊያ ተንተርሶ በምድር የተተከለ መሰላል ወደ ሰማይ ደርሶ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ቢመለከት ቤቴል ብሎ ስለጠራው ስፍራ እንዲህ አለ፡-ፈራ፥ እንዲህም አለ፦ ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም ይህም የሰማይ ደጅ ነው።"(ዘፍ.28፥17)
✅እንግዲህ ልብ አድርጉ ወደ ሎጥ ቤት መላእክትና ጻድቅ ሎጥ እንደገቡ በቤተክርስቲያንም ጻድቃኑ ቅዱሳኑ
አይታጡምና ልበ አምላክ ንጉሥ ዳዊት"ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት ወደ እርስዋ ጻድቃን ይገባሉ።" እንዳለ (መዝ.117፥20) በዚያውም ላይ መላእክት ሎጥን ወደ ቤት አግብተው በሩን እንደዘጉ ምዕመናንም ለነፍስ ወደብ መከራውን መሻገርያ በምትሆን ቤታቸው በቅዱሳን መላእክት ተጠብቀው ይኖራሉና ልዑለ ቃል ነቢይ ኢሳይያስ እንዲህ እንዳለ "ሕዝቤ ሆይ፥ ና ወደ ቤትህም ግባ፥ ደጅህን በኋላህ ዝጋ ቍጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ። "(ኢሳ.26፥20)
✅ምንም ክፉዎች ቢከቧት እና ይህችን ደጅ ቢታገሏትም በመላእክት አዋጅ ጻድቃን እስኪድኑ የሰዶም ደይን ምሳሌው በሆነ በገሃነም እሳት ኃጥአን እስኪቀጡ ቤተ ክርስቲያን መጠለያችን ናት:: ሊቁ መጋቤ ምስጢር ወርቅነህ ውቤ "ቤተ ክርስቲያን የሥጋ አጥር ናት፤ ከውስጥ ውሻ ከውጪ ጅብ የሚዘነጥላት" እንዳሉት፡ ከውስጥ እንደ ብእሲተ ሎጥ ያሉ ሐሳባቸውን ያላጠሩ (ጨው ለመበደር ወደ መንደር ስትሄድ የእንግዶቹን መግባት ለሰዶማውያን ነግራለችና) የቤተ ክርስቲያንን ፈተና የሚያከብዱ በኋላ ሐውልተ ጼው ሆነው የቀሩ፤ ከውጪ እንደ ሰብአ ሰዶም ቅዱሳኑን ተጋፍተው ደጁን ሊያጠፉ የሚዳክሩትን ኋላ ከሰማይ በዘነበ እሳትና ዲን የጠፉትን ታግሣ የምትቆይ ይልቁንም ለክርስቶስ ሁሉን እንዲህ ብላ የምታቀርብ "አሮጌው ከአዲሱ ጋር፥ በደጃችን አሉ ውዴ ሆይ፥ ሁሉን ለአንተ ጠበቅሁልህ።" መኃ.7፥14 "ምንም በየዘመናቱ የሚነሳው መከራ ቢያልፍም ቤተ ክርስቲያን ግን አታርፍም" እንዲሉ ክብርና ጌጧ የቅዱሳን መገፋት የሆነ ሊቁ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ "ሰማዕትኒ ያሰረግዋ ለቤተ ክርስቲያን በገድሎሙ"ብሎ የመሰከረላት ቤት ናት::
✅በተለይ ዛሬ በዘመናችን ይህችን ደጅ ሲፈልጉ የሚደክሙ ለማፍረስ የሚሰበሰቡ ነገር ግን የወደቁ መሳርያ የሚተክሉ ነገር ግን የማይከናወንላቸው ብዙዎች ናቸው። አጽንቶ የሠራት አስውቦም የሸለማት ፈጣሪዋ ይጠብቃታልና ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ይህን እንዲህ እያለ ያስረዳናል፡- "እነሆ፥ ድንጋዮችሽን ሸላልሜ እገነባለሁ፥ በሰንፔርም እመሠርትሻለሁ። የግንብሽንም ጕልላት በቀይ ዕንቍ፥ በሮችሽንም በሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ዳርቻሽንም ሁሉ በከበሩ ድንጋዮች እሠራለሁ። ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፥ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል።
✅እነሆ፥ ይሰበሰባሉ፥ ነገር ግን ከእኔ ዘንድ አይሆንም በአንቺም ላይ የሚሰበሰቡ ሁሉ ከአንቺ የተነሣ ይወድቃሉ።... በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም በፍርድም በሚነሣብሽ ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፥ ጽድቃቸውም ከእኔ ዘንድ ነው፥ይላል እግዚአብሔር (ኢሳ 54፥11-17)እንግዲህ ተመልከቱ! እንኳን ሥጋን ለብሰው የሚያሴሩ ደካሞች ይቅርና በከንቱ ይደክማሉ እንጂ ይህች ደጅ ኋላም ቢሆን የገሃነም ደጆች የማይችሏት ይህች ደጀ ሰማይ ደጀ ቤተ ክርስቲያን ናት ክርስቲያን።"እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። (ማቴ.16፥18)
✅ #እመቤታችን ( )ሁለተኛዋ ደጅ የሰላም አለቃ የዘለዓለም አባት ጌታችንንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገባባት ማደርያው ደጀ ሰላም ድንግል ማርያም ናት:: ነቢዩ ሕዝቅኤል እንዲህ ሲል እንዳሳወቀን፡- "ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር።እግዚአብሔርም፦ ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፥ ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል።አለቃው ግን እርሱ በእግዚአብሔር ፊት እንጀራ ይበላ ዘንድ ይቀመጥበታል በበሩ ደጀ ሰላም መንገድ ይገባል በዚያም መንገድ ይወጣል።"(ሕዝ 44፥1-3)
✅ይህንንም ሊቁ ማር ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ "ኆኅትሰ ድንግል ይእቲ"ብሎ መድኃኒታችንን የወለደች ድንግል ቅድመ ወሊድ ቢሉ ድኅረ ወሊድ ጊዜ ወሊድም በድንግልና ኖራለችና ደጀ ሰላም ያለው እርሷን ነው ይለናል::እግዚአብሔር በጸጋ የተገለጸባቸው ብዙ ማደርያ ድንኳኖች ከያዕቆብ ቤት ተገኝተዋል፡፡ ይሁንና ግን አምባ መጠጊያችን የምትሆነን ድንግልን ለኩነት ማደርያነት መርጧታልና ደጆችዋን ከሁሉ ይልቅ ይወዳቸዋል"ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ፥ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወድዳቸዋል "(መዝ. 86፥2)
✅ዛሬ ግን ትውልዱ የራሱን ጽድቅ ሲመሰክር ለድንግሊቱ ክብር አንደበቱ ሲታሰር ይታያል::ይህን የሰላም አለቃ የዘለዓለም አባት አምላክ ሳለ አማላጅ የሚል "የሚረግም" ይህችን የሰላም ደጅ ፈጣሪን የወለደች የዓለም እናት ትውልድ ሁሉ ያመሰግነኛል ብላ ሳለች የማይባርካትን ትውልድ ከነቅጣቱ በፈታኂው ንጉሥ መፍቀሬ ጥበብ እንዲህ ተዳኝቶ ተቀምጧል:: "አባቱን የሚረግም፥ እናቱንም የማይባርክ ትውልድ አለ። ለራሱ ንጹህ የሆነ የሚመስለው ከርኵሰቱ ያልጠራ ትውልድ አለ። ከፍ ከፍ ያሉ ዓይኖች ያሉት፥ ሽፋሽፍቶቹም ወደ ላይ የሚያዩ ትውልድ አለ።""በአባትዋ የምታላግጥን የእናትዋንም ትእዛዝ የምትንቅን ዓይን የሸለቆ ቍራዎች ይጐጠጕጡአታል፥ አሞራዎችም ይበሉአታል (ምሳ.30፥11፥13,17)
✅ይልቁንም በደጃፉ የተጉ ግን ዓይናቸው አንሥተው አምላካቸውን ከእናቱ ጋር ያያሉ "ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ወድቀውም ሰገዱለት፥" (ማቴ. 2፥11) ከገሀነም እሳትና ደይን አምልጠው ሕይወትንና ሞገስን አግኝተው በብሔረ ተድላ ለዘለዓለም ይኖራሉ "ትምህርቴን ስሙ፥ ጠቢባንም ሁኑ፥ ቸል አትበሉትም። የሚሰማኝ ሰው ምስጉን ነው፤ ዕለት ዕለት በቤቴ መግቢያ የሚተጋ፥ የደጄንም መድረክ የሚጠብቅ። እኔን ያገኘ ሕይወትን ያገኛልና። ከእግዚአብሔርም ሞገስን ያገኛልና።" (ምሳ 8፥34)
✅እንደ መደምደሚያም ቀጣዩን የንሰሐ ጥሪ ከኑሲስ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ በማውሳት ትምህርታችንን እንቋጫለን፡- “ወናጽምዖ ለዘይጼውአነ እንዘ ስፉህ እዴሁ ኀቤነ እምቅድመ ኅልፈተ ዕለት ወናፍጥን ወንግድፍ ርእሰነ ቅድሜሁ እንዘ ንብል ናሁ አበስነ በቅድሜከ እግዚኦ ነጽር ኃቤነ ወኢትግድፈነ ዘልሕኩትከ እስመ ግብረ እደዊከ ንህነ እስመ አልቦ በውስተ ሞት ዘይዜከረከ ወበሲኦልኒ መኑ ዘየአምነከ ንትባደር ለንሰሃ. ዘመናችን ሳይፈጸም እጁን ወደኛ ዘርግቶ የሚጠራንን እንስማው፡፡ ፈጥነን በፊቱ ራሳችንን እናዋርድ፡፡አቤቱ እነሆ አንተን በድለናል፤ እኛን በዓይነ ምሕረት ተመልከት፤ ፍጥረቶችህን አትጣል፤ የእጅህ ፍጥረቶች ነንና ከሞት በኋላ የሚያስብህ በመቃብርስ ተስፋ የሚያደርግህ ማነው እያልን ፈጥነን ንሰሐ እንግባ” (ሃይ.አበ. ም.37፥11)፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።
Click here to claim your Sponsored Listing.
Category
Address
Peda
Bahir Dar
1216