Awash Subah brodcast
I was born to be Ethiopian, I am Ethiopian, I will die for Ethiopia! ! ! I love my beloved country Ethiopiyaye! !!
08/07/2025
#የስልካችንን የሶፍትዌር ቨርዥን እንዴት ማወቅ እንችላለን?
የኤሌክትሮኒክስ ምርት አምራች ኩባንያዎች በየጊዜው የዲቫይሶች ማንቀሳቀሻ ሶፍዌር ስሪት ላይ ማሻሻያ ያደርጋሉ፡፡ በተለይ የስልክ አምራች ኩባንያዎች የሶፍትዌር ስሪት (software version) በፍጥነት በሚባል ደረጃ ሲያወጡ እናስተውላለን፡፡ አፕል በሉት ሳምሰንክ አልያም ሶኒ ሁሉም የስልክ አምራች ኩባንያዎች ቢያንስ በአመት አንዴ የስልክ ሶፍትዌር ስሪት ማሻሻያዎችን ያወጣሉ፡፡
እነዚህን ማሻሻያዎች መጫን በአይናችን ከማናያቸው የስልካችንን ቅልጥፍና ከፍ ከሚደርጉ ማሻሻያዎች እስከ አፕሊኬሽን ማዘመንና ቅየራ ይደርሳሉ፡፡ አንዳንዴ ስልካችንን አፕዴት አድርገን ምንም አይነት ለውጥ ላናይበት እንችላለን ነገር ግን አሰራሩን የሚያዘምኑ ውስጣዊ ማሻሻያዎች እንዳደረገ ግን መገመት እንችላለ፡፡
ለመሆኑ የስልካችንን አዲስ የሶፍትዌር ቨርዥን መጫን ምን ጥቅም ያስገኛል?
የአይከኖች ለውጥ፣ የስክሪን አቀማመጥና ሌሎች የሚታዩ ክፍሎች ለውጥ
አዲስ አፕሊኬሽኖች ወይም አዲስ ገጽታ
ከዚህ ቀደም የነበሩ ገጽታዎች ላይ የሚደረግ ለውጥ
የሴኪዩሪቲ ማሻሻያዎች
የስልካችንን የመስራት አቅም የሚያሻሽሉ ድብቅ ማሻሻያዎች
ወ.ዘ.ተ
የስልኬን የሶፍትዌር ስሪት እንዴት ማወቅ እችላለሁ?
ለሳምሰንግ (Samsung)
ሴቲንግ ውስጥ እንገባና About Device ወይም About Phone የሚል ፈልገን እንከፍተዋለን፡፡
ከሚመጡል ዝርዝሮች መካከል Android version የሚለው ዝርዝር ውስጥ የሶፍትዌር ስሪታችንን ማግኘት እንችላለን፡፡
ለአይፎን (iPhone)
ሴቲንግ ውስጥ እንገባና General የሚለውን እንከፍታለን፡፡
በመቀጠል About
About የሚለው ዝርዝር ውስጥ IOS Version የሚለው ትይዩ የሶፍትዌር ስሪታችንን እናገኛለን
08/07/2025
#ጽዮናዊነት ምንድን ነው?
ጽዮናዊነት በአውሮፓ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው። ፍልስጥኤም በምትባለውም ምድር የአይሁድ አገርን መመሥረት ዋነኛ ግቡ ነው። ይህ እንቅስቃሴ የአይሁዳውያን የጥንት ርስት ናት የሚሏትን የአይሁዳውን አገር የሆነች እስራኤል ፍልስጥኤም ተብሎ በሚታወቀው መሬት የመመሥረት ፍላጎት የነበረው ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ፍልስጥኤም ለሁለት ተከፍላ የአይሁዶች እና የአረቦች የተናጠል አገራት አንዲመሠረቱ ሃሳብ አቀረበ። በአውሮፓውያኑ 1948ም እስራኤል በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ በአገርነት መመሥረቷ ታወጀ።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ከቀያቸው እና ከቤታቸው ተፈናቀሉ። ከዚያም በኋላ እ.አ.አ በ1967 የተደረገውን የስድስቱን ቀን ጦርነት ተከትሎ የፍልስጥኤም ግዛቶች የሚባሉትን ዌስት ባንክን እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን እስራኤል በኃይል ተቆጣጥራ ትገኛለች። ባለፉት አምስት አስርት ዓመታትም በነዚህ ግዛቶች የአይሁዶች የሰፈራ መንደሮችን አቋቁማለች። 700 ሺህ የሚቆጠሩ አይሁዳውያን በእነዚህ ስፍራዎች አስፍራለች።
የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት እስራኤል በቁጥጥሯ ስር ባሉ ግዛቶች የሰፈራ መንደሮችን ማቋቋሟ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጻረር እና ሕገወጥ ነው ሲሉ ይጠሩታል። የእስራኤል መንግሥት ምሥረታ በፍልስጥኤም የሚኖሩ አረቦችን መብት የነፈገ መሆኑን በመጥቀስ ፍልስጥኤማውያን እንዲሁም ሌሎች አረቦች ይቃወሙታል።
የጽዮናዊነትን እንቅስቃሴ የሚያቀነቅኑ አካላት እስራኤል እንደ አይሁድ ግዛትነቷ ጥበቃ ሊደረግላት እንዲሁም ልትስፋፋ ይገባል ብለው ያምናሉ። አንዳንድ ጽዮናውያን እስራኤል ካላት ግዛት በተጨማሪ ሌሎች ግዛቶችንም የመቆጣጠር መብት አላት ብለው የሚከራከሩ ሲሆን፣ ሌሎች በዚህ ሃሳብ አይስማሙም። አብዛኛው አይሁዳውያን ጽዮናውያን ቢሆኑም፣ ጥቂቶች በፖለቲካዊ እና በሃይማኖታዊ ምክንያቶች ጽንሰ ሃሳቡን ይቃወማሉ። አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች ጽዮናዊነትንም ማቀንቀን ይችላሉ።
08/04/2024
የ ቬትናም ጦርነት (The vietnam war)
“ልዕለ ኃያሏ” ሀገር አሜሪካ ሽንፈትን ቀምሳ ከወጣችበት ጦርነቶች መካከል በታሪክ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። የቬትናም ጦርነት! ይህ ከሶስት ሚሊዮን በላይ የሚሆን ክቡር የሰው ልጅን ህይወት ያስገበረው ጦርነት፣ አፍጋኒስታን ላይ እንደታየው አሜሪካ በመጨረሻ ማለቂያ የሌለውን ጦርነት ጥላ እንድትሸሽ እንድትወስን ያስገደዳት ጦርነት ነበር። ያውም ሃምሳ ስምንት ሺህ ወታደሮቿን በሞት ተነጥቃ። አሜሪካ ቬትናምን ለቃ የወጣችው በፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ውሳኔ እ.አ.አ በ1973 ዓ.ም. ነበር።
#ጦርነቱ እንዴት ተጀመረ?
በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በደቡብ ምስራቅ ኢሲያ በኢንዶቻይና ባሕረሰጤ የምትገኘው ሀገር ቬትናም በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስር ነበረች። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ግዜ ጃፓን ቬትናምን ስትወር በቻይና እና በሶቪዬት ህብረት ኮሚኒስት ርዕዮት መንፈስ የነቃው የቬትናሙ ሆ ቺ ሚኒ ሀገሩን ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ብሎም ከጃፓን ወረራ ነጻ ለማውጣት የሀገሩን ልጆች አስተባብሮ ተነሳ። የዚህ አብዮተኛ ስም በኢትዮጵያ የተማሪዎች ትግል ውስጥ ሲጠቀስ የምንሰማበትም ምክንያት አልበገር ባይነቱ ነው።
ፋኖ ተሰማራ
ፋኖ ተሰማራ
እንደ ሆ ቺ ሚኒ
እንደ ቼ ጉቬራ!
ጃፓን ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ስትሸነፍ ጦሯን ከቬትናም ብታስወጣም በBao Dai የሚመራ የሞግዚት አስተዳደር በቬትናም አስቀምጣ ነበር። በሆ ቺ ሚኒ የሚመራው ኃይል ግማሹን ቬትናም ሲቆጣጠር የጃፓኑ የሞግዚት አስተዳደር ደግሞ የተቀረውን በመያዝ መላውን ቬትናም አንድ አድርጎ ለመግዛት የሚደረገው ፍጥጫ ቀጠለ። የሁለቱ መሪዎች መሰረታዊ ልዩነት የርዕዮተ ዓለም ነበር። ሆ ቺ ሚኒ ኮሚኒስት ቬትናምን የመመስረት ሃሳብ የሰነቀ ሲሆን ፣ በተቃራኒው ፈረንሳይ የተማረው ባኦ ዳይ ሀገሩን በምዕራባዊያኑ ሞዴል የመገንባት ዓላማ ነበረው። የአንድ ሀገር ልጆች ግን ሁለት የሚቃረኑ የፖለቲካ አመለካከቶች! በዚህም ምክንያት ቬትናም ደቡብ እና ሰሜን ተብላ ለሁለት ተከፈለች።
እዚህ ጋር ነው እንግዲህ አሜሪካ የምትመጣው። ቀዝቃዛው ጦርነት እየተፋፋመ ሲመጣ የአሜሪካው የወቅቱ ፕሬዝዳንት Dwight D. Eisenhower ማንኛውም ከሶቪዬት ህብረት ጋር የተባበረን ኃይል በጠላትነት በመፈረጅ ድጋፋቸውን ለደቡብ ቬትናም እንደሚሰጡ ተናገሩ። አሜሪካ በጊዜው Bao Daiን ከስልጣን በማስወገድ (በምርጫ?) የሰሜን ቬትናምን ስልጣን ለተቆጣጠረው Ngo Dinh Diem የስልጠና እና የመሳሪያ ድጋፍ ማድረጓን ቀጠለች። የሰሜኑ ኃይልም viet cong እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት እና በሆ ቺ ሚኒ ይመሩ የነበሩት ኮሚኒስት ኃይል ላይ ከፍተኛ ጫና እና ጥቃት ማድረስ ጀመረ። ይሁንና viet cong በቀላሉ የሚፈታ ኃይል ሊሆን አልቻለም።
#የልዑኩ ምክር
እ.አ.አ በ1961 ዓ.ም. የቬትናምን ሁኔታ ገምግሞ ሪፖርት እንዲያደርግ የተላከው ልዑክ ወደ አሜሪካን ሲመለስ ለፕሬዝዳንት ኬኔዲ ያቀረበው ሃሳብ ሰፋ ያለ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን ያካተተ ነበር። ይሁንና ኬኔዲ ወታደራዊ እርዳታው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቢወስኑም የአሜሪካን ወታደር በብዛት ወደ ቬትናም የመላኩ ጉዳይ ላይ ብዙም አልገፉበትም። በኬኔዲ ዘመን በቬትናም የነበረው የአሜሪካ ወታደር ቁጥርም ከአስር ሺህ ያነሰ ነበር።
በ1963 ዓ.ም. Ngo Dinh Diem በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣናቸው ሲወርዱ ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲም በተተኮሰባቸው ጥይት ተገደሉ። የኬኔዲን ሞት ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጡት Lyndon B. Johnson የአሜሪካን ጦር በቬትናም ወደ ለየለት ጦርነት እንዲገባ አደረጉት።
#በ1965 ዓ.ም. 82,000 የአሜሪካን ወታደሮች በቬትናም ጦርነት ቢዘምቱም ጦርነቱን ማሸነፍ ግን አልቻሉም። ይልቁንም በቬትናም የነበሩ የጦር መሪዎች ጦርነቱን ለማሸነፍ ተጨማሪ 175,000 ወታደር ያስፈልገናል ሲሉ የአሜሪካን መንግስት ጠይቀዋል። በሀገረ አሜሪካ ጦርነቱን የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎች ኣየበረቱ ቢመጡም ፕሬዝዳንት ጆንሰን ከገቡበት ጦርነት ያወጣናል ብለው በማሰብ በሁለት ዙር 200,000 የአሜሪካን ወታደሮች ወደ ቬትናም እንዲዘምት ትዕዛዝ ሰጡ።
በ1967 ዓ.ም. ገደማ በቬትናም የነበርው የአሜሪካ ወታደር ቁጥር ወደ 500,000 ቢጠጋም ይህ ነው የሚባል ድል ግን ማስመዝገብ አልቻለም ነበር። አሜሪካ ከምታስመዘግበው ድል ይልቅ በየዕለቱ በየጦር ግንባሩ የሚወድቅ ወታደሯን ማንሳት እና መቁጠር ሆነ ዜናው ሁሉ። ይህን የሰሙ አሜሪካዊያን ልጆቻችንን መልሱልን፣ ቬትናምን ለቬትናማዊያን ተውላቸው፣ ከቬትናም ውጡ ሲሉ አደባባይ ወጡ።
ቀጣዮቹ የጦርነት ዘመናት ለአሜሪካን ወታደሮች በአካል እና በስነ ልቦና የተጎዱባቸው ግዜዎች ነበሩ። አብዛኛው ወታደር ለስነ ልቦና ቀውስ ሲዳረግ አያሌዎቹ ደግሞ አደንዛዥ እጽ ተጠቃሚዎች ሆኑ፣ ለpost-traumatic stress disorder ተጋለጡ።
ፕሬዝዳንት ኒክሰን ወደ ስልጣን ሲመጡ የቀደመውን አስተዳደር በመውቀስ የአሜሪካን ወታደር ከቬትናም ለማውጣት እና በምትኩ የደቡብ ቬትናም ኃይሎች ራሳቸውን ችለው እንዲዋጉ ለማድረግ ውሳኔ ውሳለፉ። የዚህ እስትራቴጂ መጠሪያ ነበር Vietnamization!
“In the previous administration, we Americanized the war in Vietnam. In this administration, we are Vietnamizing the search for peace.”
#የመጨረሻዎቹ ቀናት
እንደ አውሮፓዊያኑ ዘመን አፕሪል 30 ቀን 1975 ዓ.ም Saigon በ ቬትኮንጎች እጅ ስትወድቅ የመጨረሻዎቹ አሜሪካዊያን ቬትናምን እየለቀቁ ነበር። ይህ ዕለት የቬትናምን ጦርነት ፍጻሜ ያበሰረ ዕለት ቢሆንም ለአሜሪካዊያን እድሜ ዘመናቸውን የማይፍቁት የስንፈት ታሪክ በዓለም የታሪክ መዝገብ ላይ የተፋቀበት ዕለት ነው። በዚህ ዕለት የአሜሪካ መንግሥት በቬትናም የቀሩ ዜጎቹን ኣና ወታደሮቹን በጥድፊያ በአየር ማጓጓዣዎች ለማውጣት ያደርግ የነበረው ሙከራ እና ጦርነቱን ሽሽት ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ይሞክሩ የነበሩት የቬትናማዊያን የሞት ሽረት ትግል ትዕይንት መቼም ቢሆን ከህሊና የሚጠፋ አይደለም።
03/02/2024
#ቤሊንግሃም ግሪንዉድን ‘ደፋሪ’ ብሎ ተሳድቧል ከተባለ በኋላ ላ ሊጋ ምርመራ ጀመረ
*****************
ጌታፌ ከሪያል ማድሪድ በተጫወበት ወቅት የማድሪዱ ጁድ ቤሊንግሃም የጌታፌውን ሜሰን ግሪንውድን “ደፋሪ” ሲል ሰድቦታል ከተባ በኋላ ላ ሊጋው ምርመራ ጀመረ።
ላ ሊጋው ምርመራውን የጀመረው ጌታፌ ተጫዋቹ በማድሪዱ አማካይ “ደፋሪ” ተብሎ ተሰድቧል በሚል ይፋዊ ቅሬታ ለሊጉ ካቀረበ በኋላ ነው።
ላ ሊጋው ምርመራውን የከንፈር እንቅስቃሴን የሚያነቡ ባለሙያዎችን በመቅጠር መጀመሩን ይፋ አድርጓል።
የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ የክንፍ ተጫዋች ግሪንዉድ የመድፈር ሙከራ እና አካላዊ ጥቃት የሚሉ ክሶች ቀርበውበት ከዩናይትድ ለረዥም ጊዜ ተገልሎ ከቆየ በኋላ ወደ ጌታፌ መዘዋወሩ ይታወሳል።
በክግሪንዉድ ክስ የዐይን ምስክር ተብለው ተመዝግበው የነበሩ ሰዎች እራሳቸውን ከክሱ ማራቃቸውን ተከትሎ እንዲሁም ክሱን የተመለከተ አዲስ ማስረጃ ተገኝቷል በሚል ተጫዋቹ ላይ ቀርበውበት የነበሩት ክሶች በሙሉ ውድቅ ተደርገዋል።
እንደዚያም ቢሆን ግሪንዉድ የቀረቡበት ክሶች ትልቅ ጉዳት አድርሰውበት ከዩናይትድ ካለያየው በኋላ ወደ ስፔን ፊቱን አዙሮ ጌታፌን ተቀላቅሏል።
ከትናንት በስቲያ ሐሙስ በነበረው ጨዋታ በሁለቱ እንግሊዛውያን መካከል አለመግባባቱ የተፈጠረው ቤሊንግሃም ከግሪንዉድ ኳስ ለመንጠቅ ከሞከረ በኋላ ነው። ማድሪድ ከሜዳው ውጪ 2 ለ 0 ባሸነፈበት ጨዋታ ሁለቱ ተጫዋቾች በተለያየ አጋጣሚ ሲጎሻሸሙ ታይተዋል።
ቤሊንግሃም ክስ የቀረበበትን ስድብ ሲሳደብ ይታይበታል የተባለው ተንቀሳቃሽ ምሥል በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ተሠራጭቷል።
ላ ሊጋው ክስተቱን ተከትሎ ጌታፌ ይፋዊ ቅሬታ ማስገባቱን በገለጸበት መግለጫው “ጌታፌ ለጨዋታ ዳይሬክተር ይፋዊ ቅሬታ አስገብቷል። መደበኛ የአሠራር ሂደትን በመከተል ዳይሬክተሩ ጉዳዩን ለመመርመር እና በጠንካራ ማስረጃ ላይ ተመርኩዞ እርምጃ ለመውሰድ የከንፈር እንቅስቃሴ ንባብ ሪፖርትን ጠይቋል” ብሏል።
ቤሊንግሃም ከጀርመኑ ቦሪሺያ ዶርቱሙንድ ወደ ማድሪድ በ103 ሚሊዮን ፓወንድ ክፍያ ከተዘዋወረ በኋላ በስፔን ጥሩ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። ቤሊንግሃም በ27 ጨዋታዎች 18 ጎሎችን አስቆጥሯል።
ግሪንዉድ ለአዲሱ ክለቡ ጌታፌ 21 ጊዜ ተሰልፎ 6 ጊዜ ኳስን ከመረብ አገናኝቷል።
ቢቢሲ
26/01/2024
የኢትዮጵያ መከላከያ መሥራች አጼ ምኒልክ መሆናቸውን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ተናገሩ
-----------------------------
በ116ኛው የሠራዊት ቀን ሲከበር ንግግር ያደረጉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ “ዐጼ ምኒልክ የጦር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ያቋቋሙበትን ቀን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን ኾኖ እንዲከበር ተደርጓል” በማለት ቀኑ ለምን እንደተመረጠ ይፋ አደረጉ።
ከዚህ ሌላ ፊልድ ማርሻሉ በንግግራቸው፤
ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ ከጀግኖች የተረከብናትን ኢትዮጵያ እንደተከበረች እና ማንነቷ እንደተጠበቀ ለማስቀጠል ወታደራዊ ዝግጁነታችንን አሳድገንና ቁመናችንን አዘምነን ማንኛውንም ተልዕኮ በላቀ ብቃት ለመፈጸም ሠራዊቱ ዝግጁ መሆኑን አሣውቀዋል።
የሠራዊቱ አባላት የተሠጣቸውን ታላቅ አደራ በድል ለመወጣት የመፈጸም ብቃታቸውን በማሣደግ በዓላማ ጽናታቸው እንዲቀጥሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አሳስበዋል፡፡
ሠራዊቱ ሀገሩን እና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በመጠበቅ ረገድ ሄላፊነቱን በብቃት እየተወጣ መሆኑን የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ የታጠቁ ኃይሎችን እና ኢ- መደበኛ አደረጃጀቶችን ወደ ሕጋዊ መስመር ለማስገባት እየተሠራ ያለው በሱዳን የተከሰተው ችግር በኢትዮጵያም እንዳይደገም በማሰብ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
የምድር ሃይል፣ የአየር ሃይል ፣ የባሕር ሃይል እና የሳይበር ኃይሎቻችንንም ዘመኑን እና ኢትዮጵያን በሚመጥኑ መልኩ እየገነባን የተሻለ አስተማማኝ ደረጃ ላይ ማድረስ ችለናልም ብለዋል።
የካቲት 7 ቀን 1987 ዓ.ም የሠራዊት ቀን ሆኖ እንዲከበር መወሰኑ ወገንተኝነት የፈጠረው አንዱ ታሪካዊ ስህተት መሆኑንም አንስተዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተሳሳተውን ውሳኔ በማሥተካከል የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሠራዊት እንደ ተቋም የተመሠረተበት ቀን ጥቅምት 15 እንዲሆን መወሠኑን ተናግረዋል። በመሆኑም “ዐጼ ምኒልክ የጦር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ያቋቋሙበትን ቀን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን ኾኖ እንዲከበር ተደርጓል” ብለዋል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ።
ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን (አባ መላን) የመጀመሪያው የጦር ሚኒስትር አድርገው የሾሙበት እና ሠራዊቱ ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን መሠረት የጣሉበት መሆኑን የጠቆሙት ፊልድ ማርሻሉ፣ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ሠራዊቱ ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ እንዲቀረፅ በሳል አመራርነት ሰጥተዋል ብለዋል።
116ኛው የሠራዊት ቀን ለሀገራቸው በየዘመናቱ መስዋዕት የከፈሉ ጀግኖችን የምንዘክርበት ቃላችንን የምናድስበት እና ይበልጥ ለማንኛውም ተልዕኮ የምንነሳሳበት ዕለት ነው። (የመከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም)
15/12/2023
#“በአፍሪካ የራሱ የጣት ምልክት ያለው #የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ”
☆☆☆☆▪▪▪▪▪☆☆☆☆☆
“በምልክት ቋንቋ የሚነጋገሩ ሰዎች ሲያዩ የሚያማትቡ፣ ደንግጠው የሚሸሹም ብዙዎች ናቸው” የሚለው የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ እና ጋዜጠኛው አማረ አያሌው ነው።
ስለ ምልክት ቋንቋ እንዲሁም መስማት ስለተሳናቸው ሰዎች በብዙዎች ዘንድ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ ቋንቋውን እንደ ቋንቋ ለመውሰድ የሚቸግራቸው ጥቂት አይደሉም።
አማረ ግን “የኢትዮጵያ 81ኛው ቋንቋ” ይለዋል።
በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር ምሥረታ ውስጥ ካሉ አንዱ የሆኑት አቶ ተክለሃይማኖት ደርሶ እንደሚሉት፣ በዚህ የተዛባ አመለካከት ሳቢያ ማኅበረሰቡ መስማት የተሳናቸውን ‘ራሳቸውን ችለው መኖር የማይችሉ ደካሞች’ አድርጎ ይወስዳል።
ቋንቋ ያላቸው፣ የሚግባቡ አድርጎ አለመውሰድም አለ።
ሆኖም ግን “ቋንቋ አላቸው። ቋንቋ ካለ ደግሞ ባህል አለ። ባህል ካለ ደግሞ ኩራት አለ። የማንነት ክብር ስሜት አለ” ይላሉ።
ከታዋቂ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚዎች አንዷ እስከዳር ይኩኖአምላክ እንደምትለው፣ ካለው የግንዛቤ እጥረት የተነሳ በሌሎች አገራት የምልክት ቋንቋ ያለው ተደራሽነት በኢትዮጵያ እምብዛም አይስተዋልም።
የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ብንመለከት ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ዚምባብዌን ጨምሮ 41 አገራት የምልክት ቋንቋን ብሔራዊ ቋንቋቸው አድርገዋል።
የመስማት የተሳናቸው ዩኒቨርስቲዎችም ተጠቃሽ ናቸው።
በተለያየ ዕድሜ ላሉ ሰዎች የተዘጋጁ የምልክት ቋንቋ መማሪያ መጻሕፍት እና መዝገበ ቃላትም ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ በ1960ዎቹ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር ከተመሠረተ በኋላ ነው መዝገበ ቃላት ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው።
ይህ ዘገባ የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋን እንዲሁም የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላትን ይዳስሳል።
■‘መስማት የማትችል ከሆንክ እንዴት ልትማር ነው?’
አቶ ተክለሃይማኖት ደርሶ በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር ምሥረታ ውስጥ ካሉ መካከል አንዱ ናቸው።
በ1963 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲገቡ “መስማት የማትችል ከሆንክ እንዴት ልትማር ነው?” መባላቸውን ያስታውሳሉ።
ይህንን የተዛባ አመለካት ከግንዛቤ እና ከመረጃ ክፍተት ጋር ያስተሳስሩታል።
በምልክት ቋንቋ ረገድ፣ ከሌሎች አገራት አንጻር ሲታይ “እኛ ገና ዳዴ የምንል ጀማሪዎች ነን” ይላሉ።
ለምሳሌ በአሜሪካ መስማት የተሳናቸው ዩኒቨርስቲ የሆነው ጋሎዴት የተከፈተው ከ159 ዓመት በፊት ነው።
በአፍሪካ ውስጥ በደቡብ አፍሪካ የተሻለ ተሞክሮ እንዳለ ይነገራል።
“በቅርብ ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምልክት ቋንቋ እና መስማት የተሳናቸው ባህል መጠናት መጀመሩ ተስፋ ሰጭ ነው” ይላሉ አቶ ተክለሃይማኖት።
በቀደሙት ዓመታት መስማት የተሳናቸው እንደ አሁኑ በአደባባይ በምልክት ቋንቋ ለመነጋገር አይደፍሩም ነበር።
“ያለ ምንም መሸማቀቅ ሽንጣቸውን ገትረው በምልክት ቋንቋቸው የሚነጋገሩበት ጊዜ አልነበረም። መንገድ ላይ እየሄዱ ሳለ ሰው ሲቀርባቸው፣ እስኪያልፍ ድረስ ንግግራቸውን ገታ ያደርጉ ነበር” ሲሉ ያስታውሳሉ።
በዚያ ወቅት የነበረውን ሁኔታ አቶ ተክለሃይማኖት ሲገልጹ “. . .እንዲያውም መስማት የተሳናቸው ‘ደናቁርት’ እየተባሉ የሚጠሩበት ጊዜም ነበር። በወቅቱ በመንግሥት የተቋቋመ አንድም መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት አልነበረም” በማለት ነው።
*ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል በነበረችበት ወቅት ከኖርዲክ አገራት እና ከአሜሪካ በመጡ ሚሲዮናውያን የተቋቋሙ መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤቶች በአዲስ አበባ ሁለት እና በከረን ደግሞ አንድ ነበሩ።
ያኔ በአዲስ አበባ የአሜሪካ የምልክት ቋንቋ በኤርትራ ደግሞ የኖርዲክ የምልክት ቋንቋ ነበር የሚጠቀሙት።
በተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል መስማት የተሳናቸው ለመግባባት የሚጠቀሙበት ቋንቋ ወጥነት ባለው ሁኔታ የምልክት ቋንቋ ሆኖ የተጀመረው ሚሲዮናውያን ትምህርት ቤት ከከፈቱ በኋላ መሆኑን ያስረዳሉ።
መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር በ1963 ዓ.ም. እስከሚመሠረት እንዲህ ቆይቷል።
ማኅበሩ ሲመሠረት ከትምህርት ቤት በዘለለ መስማት የተሳናቸው የሚገናኙበትም ሆነ።
“ያኔ በኢትዮጵያ የፊደል የጣት ምልክት አልነበረም” ይላሉ አቶ ተክለሃይማኖት።
ከዚያም የማኅበሩ ሦስት መሥራቾች ያዘጋጁት የጣት ምልክት በ1967 ዓ.ም. ለያኔው የትምህርት ሚኒስትር ቀረበ። በትምህር ቤቶች ጥቅም ላይ እንዲውልም ተፈቀደ።
በኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ከመዘጋጀቱ በፊት አብዛኛው የማኅበረሰቡ ክፍል “መስማት የተሳናቸው መማርም ሆነ መሥራት ይችላሉ ብሎ የማያስብበት ጊዜ ነበር” ሲሉ ያስታውሳሉ።
■‘መዝገበ ምልክት’
አቶ ተክለሃይማኖት የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላት ከሚለው ይልቅ ‘መዝገበ ምልክት’ የሚለውን አገላለጽ ይመርጣሉ።
እንደ ማንኛውም ቋንቋ ተሰንዶ መዘጋጀቱ ለጥናት እና ለምርምር እንዲሁም ቋንቋውን መማር ለሚፈልጉ ይረዳል ይላሉ።
“መዝገበ ምልክቱ መኖሩ መስማት የተሳናቸው የራሳቸው ቋንቋ ያላቸው፣ ባህል ያላቸው አድርጎ እንዲመለከት ያግዛል” በማለት ነው የሚያስረዱት።
“ቋንቋ ካለ ባህል አለ። ባህል ካለ ደግሞ ኩራት አለ። የማንነት ክብር ስሜት አለ። ማንም በራሱ ቋንቋ ሲያናግሩት ደስታ እንደሚሰማው ሁሉ፤ መስማት የተሳናቸውም በራሳቸው ቋንቋ የሚያናግራቸው ሲያገኙ ከፍተኛ ደስታ ይሰማቸዋል። ለተናጋሪውም ትልቅ አክብሮት ይሰጣል።”
ሆኖም የምልክት ቋንቋ፣ ቋንቋ መሆኑን የማይገነዘቡ እንዳሉ ይናገራሉ።
በአንድ ወቅት የልጃቸው አስተማሪ ምልክት ቋንቋ ‘ቋንቋ’ አይደለም ማለቱን ልጃቸው እንዴት በብስጭት እንደነገራቸው እና በነገታው ስለ ቋንቋው አስረጂ ጽሑፎች ይዘው ለትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር መስጠታቸውን አይረሱትም።
እንደ ማንኛውም ቋንቋ ‘መዝገበ ምልክት’ መኖሩ፣ በቴክኖሎጂ ዕድገት ምክንያት የሚፈጠር የባህል እና የአኗኗር ዘይቤ ለውጥን ተከትሎ ከጥቅም ውጪ የሚሆኑ ቃላት እንዳይረሱ ለማድረግም ይረዳል ይላሉ።
በየጊዜው የሚፈጠሩ አዳዲስ ምልክቶች በመጽሐፍት ተሰንደው መካተት እንዳለባቸውም ያክላሉ።
■‘81ኛው የኢትዮጵያ ቋንቋ’
አማረ አያሌው የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ እና ጋዜጠኛም ነው። በኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላት ፕሮጀክት ውስጥ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ እና አስተባባሪም ነው።
“አምስት ሚሊዮን የሚገመቱ መስማት የተሳናቸው የሚጠቀሙበት ቋንቋ እንደመሆኑ ተሰንዶ መቀመጡ እንደ ቅርስ ነው” ሲል ነው መዝገበ ቃላቱን የሚገልጸው።
የመጀመሪያው ‘ሀ’ የተባለው መጽሐፍ የታተመው በ1960ዎቹ ነበር። በቀጣይ ‘ለ’ የሚል መጽሐፍም ታትሟል። ከዚያም በተለያዩ ዓመታት ለምሥራቅ እና ለደቡብ አፍሪካ አገራት ድጋፍ ሲሰጥ መዝገበ ቃላት ታትመዋል።
በቅርቡም ከፊንላንድ በተሰጠ ድጋፍ የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላት ታትሟል።
መጽሐፉ በፎቶ የምልክት ቋንቋ ምልክቶችን የሚያሳይ ነው። 2500 ፎቶዎች እና 1300 ምልክቶች የያዘ ነው።
“በምልክት ቋንቋ ለመግባባት አቅጣጫ፣ እንቅስቃሴ፣ የፊት አገላለጽ፣ ምልክት የሚደረግበት የሰውነት ክፍል በዚህ መጽሐፍ ተካተዋል” ሲል ነው አማረ የሚገልጸው።
መጽሐፉ በዋናነት መስማት ለተሳናቸው፣ መስማት ለተሳናቸው ቤተሰቦች እና ለሕዝብ አገልግሎት ሰጪዎችም እንደሚረዳ ይናገራል።
“መስማት ከተሳናቸው ጋር ለመግባባት ያግዛል። አካታችነትን ያረጋግጣል። ቋንቋውንም ከትውልድ ትውልድ ያሻግራል” ይላል።
ይህንን መጽሐፍ የክልል ዩኒቨርስቲዎች እና የመንግሥት ተቋማት ለማከፋፈል መሞከራቸው ፍላጎቱ እንዳለ ቢያሳይም ውስንነቱ ግን እንዳለ ነው።
‘81ኛው የኢትዮጵያ ቋንቋ’ በማለትም ነው አማረ የሚጠራው።
ይህ ምልክት በአሜሪካ የምልክት ቋንቋ 'ጨዋታ' ማለት ነው
የየአገሩ የምልክት ቋንቋ የተለያየ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም የተለየ የምልክት ቋንቋ አለ።
በሌሎች አገራት የምልክት ቋንቋን የሕክምና እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎችም ይማራሉ።
አሜሪካንን እንደ ምሳሌ ብናነሳ የምልክት ቋንቋ ሦስተኛ በስፋት የሚነገር ቋንቋ ነው።
“የራሱ የሆነ የጣት ምልክት ያለው የአፍሪካ ቋንቋ የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ ነው። ግን አልተነገረለትም” ይላል አማረ።
በዓመታት ሂደት ስለ ምልክት ቋንቋ ያለው ግንዛቤ መሻሻሉ ባይካድም አሁንም ክፍተቶች መኖራቸው እሙን ነው።
“. . .መስማት የተሳናቸው ባህል ላይ ጥናት ሳደርግ በ13ኛው ክፍለ ዘመን መስማት የተሳናቸው ለመሰባሰብ መሞከራቸውን የሚያሳይ መረጃ ሁሉ አግኝቻለሁ” ሲል አማረ ይናገራል።
ማኅበረሰባዊ ዕውቅና ሊሰጠው እንደሚገባም ያክላል።
“ካለው የአመለካከት ክፍተት የተነሳ የምልክት ቋንቋ ሲያዩ የሚያማትቡ፣ ደንግጠው የሚሸሹም አሉ” የሚለው አማረ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቭዢን በምልክት ቋንቋ ዜና መተላለፍ ከጀመረ በኋላ ለውጥ መታየቱን ያስታውሳል።
በብሔራዊ ቴሌቪዥን መታየት ከጀመረ በኋላ እንደ መደበኛ መግባቢያ ቋንቋ መታየት እንደጀመረም ይናገራል።
የምልክት ቋንቋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መሰጠት መጀመሩ እና በመስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበርም ሥልጠናዎች መዘጋጀቱ የመሻሻሉ አካል አድርጎ ነው የሚወስደው።
ሆኖም ግን መስማት የተሳናቸውን ማግለል አሁንም መሰናክል ነው።
“መሥራት እየቻሉ መሰናክሎች ስለበዙባቸው ከሥራ ውጪ ይሆናሉ። መስማት የተሳናቸው በቋንቋቸው ተምረው መሥራት የሚችሉበት መንገድ መመቻቸት ያለበት ለዚህ ነው።”
የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር ከተመሠረተ 52 ዓመታት ቢያስቆጥርም የገንዘብ እና የሰው ኃይል ውስንነቱ እንዳለ ነው። ማኅበሩን ማጠናከር የራሱ ሚና እንደሚኖረው አማረ ያምናል።
በኢትዮጵያ ቋንቋው እንዲስፋፋ መስማት የተሳናቸው እንዲሁም የተቀረው ማኅበረሰብ ተካታችነትንም እንደሚያሻ ያክላል።
“የምልክት ቋንቋ በማስተርጎሜ በጣም ደስተኛ ነኝ”
በኢቢሲ የምልክት ቋንቋ ክፍል የምትሠራው እስከዳር ይኩኖአምላክ በአገሪቱ ከታዋቂ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚዎች መካከል አንዷ ናት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ2002 ዓ.ም. የምልክት ቋንቋ ትምህርት ክፍል ገብታ ከተማረች በኋላ ኢቢሲን ጨምሮ በሌሎችም መድረኮች በምልክት ቋንቋ አስተርጓሚነት ሠርታለች።
የዩኒቨርስቲ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለች ጀምሮ ላለፉት 10 ዓመታት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥም በአስተርጓሚነት እየሠራች ትገኛለች።
አሁን ያለችበት ከመድረሷ በፊት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳለች በዓመቱ ትምህርት ክፍል ልቀይር ይሆን? እያለች ታስብ እንደነበር ታስታውሳለች።
“የምልክት ቋንቋ ትምህርት ክፍል ሲደርሰኝ እንዴት እንደምማር እና እንደምግባባ ፈርቼ ነበር” ትላለች።
ቆይታ ግን ሐሳቧን ለወጠች። “ነገር ግን የምልክት ቋንቋን ቶሎ ነበር የቻልኩት። ዶርም ውስጥም ሰባት መስማት የተሳናቸው ከእኔጋ ነበሩ። ከእነሱ ጋር ስውል ሳድር ቋንቋውን ቻልኩ።”
በሌሎች አገራት ቋንቋው ካለው ተደራሽነት አንጻር የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ ውስነት አንደኛው ምክንያት የግንዛቤ እና የዕውቀት አለመኖር መሆኑን እስከዳር ትናገራለች።
“የሥራ ዘርፍን ብንመለከት እንኳን ከ70 በመቶ ያላነሱት መስማት የተሳናቸው በእንጨት ሥራ ይሰማራሉ። በሙያው ውጤታማ ቢሆኑም በሌሎች ዘርፎች ተቀጥረው ለመሥራ ሲሞክሩ የሚቀጥራቸው ስለማይኖር ነው አንድ ሙያ ብቻ የሚመርጡት” ትላለች።
መስማት የተሳናቸውን ሥራ መቅጠር አብሮ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ መቅጠር እንደሚያስፈልገው በማሰብ ተቋማት ለመቅጠር እንደማይፈቅዱ ትናገራለች።
መስማት የተሳናቸው ‘አይችሉም’ በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ በተለያዩ መድረኮች ላይ እንዳይሳተፉ እንደሚገፉም እስከዳር ትጠቅሳለች።
ለዚህም ነው የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላት አስፈላጊነትን አጽንኦት የምትሰጠው።
የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላት መኖሩ አንዳንድ ከረዥም ጊዜ በኋላ የሚዘነጉ ወይም የሚጠፉ የምልክት ቋንቋዎች እንዳይረሱም አስተርጓሚዎችን ይረዳል ትላለች።
ሆኖም መዝገበ ቃላቱ ተደራሽነቱ ውስን እንደሆነ ሳትገልጽ አታልፍም።
መስማት ከተሳናቸው ትምህርት ቤቶች እና የአካል ጉዳተኞች መገልገያዎች ከሚሸጡ መደብሮች በዘለለ አይስተዋልም።
እንደ ሌሎች የአካል ጉዳቶች በዕይታ የማይለይ መሆኑ መስማት የተሳናቸውን በተለየ ሁኔታ የሚፈትን እንደሆነ እና በምልክት ቋንቋ በቂ መረጃ አለመቅረቡም ሌላ ክፍተት እንደሚፈጥር ታስረዳለች።
ኮቪድ-19 በተነሳበት ወቅት ስለ ወረርኙ መረጃዎች በምልክት ቋንቋ አለመዘጋጀታቸው መስማት የተሳናቸውን ለሕመሙ ተጋላጭ አድርጎ እንደነበር ታስታውሳለች።
“በዚያ ወቅት ከእሑድ እስከ እሑድ በዜና ሽፋን ስሰጥ ነበር። በሥራዬ ለውጥ ካመጣችሁባቸው አንዱ ይሄ ነው” ትላለች።
“በብዛት ያለው አመለካከት የምልክት ቋንቋ ብንማርስ ባንማርስ የሚል የሚል ነው” ስትል እስከዳር ትናገራለች።
እሷ ግን “የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ” ብላ ነው የምትገልጸው።
bbc
13/12/2023
#‘በኦንላይን’ ሥራ እንዴት ገንዘብ ማግኘት ይቻላል? “በ9 ወር ሚሊየነር ሆኛለሁ” የሚለው ኢትዮጵያዊ
■■■■■■■■■■■
ናትናኤል እናቱ ‘እንጀራ ይውጣልህ’ ብለው መርቀውታል።
የማይሞክረው ነገር የለም። የማይገናኙ የሚመስሉ ሥራዎችን ይሠራል።
የእንጨት ሥራ፣ ሙዚቃ ማጫወት (ዲጄ)፣ ቪዲዮ ኤዲቲንግ፣ ግራፊክስ እና ዲዛይን፣ ዳንስ ማሠልጠን እና ዲሽ መግጠም ያውቅበታል።
*የእናቱ ምርቃት ደርሶ እንጀራ የወጣለት ግን ‘በኦን ላይን ቢዝነስ’ [በኢንተርኔት አማካይነት የሚሠራ ሥራ] ይመስላል።
በዚህ ሥራ በዘጠን ወራት ውስጥ ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘት እንደቻለ ይገልጻል።
■እንዴት?
*ናትናኤል ተፈሪ ሥራን እጅግ ይወዳል። ያለ ሥራ መቀመጥ አይፈልግም።
አባቱ በጠና ሲታመሙ ግን እርሳቸውን ለማስታመም ሥራ ማቆም ግድ ሆነበት።
ሥራ ከጀመረባት ባሕር ዳር ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ።
በዚህ መካከል፣ ጓደኛው ቤት ሆኖ ሊሠራበት የሚችለውን ድረ ገጽ ጠቆመው።
ይህ ድረ ገጽ ‘አፕወርክ’ (upwork) ይሰኛል።
በ‘አፕወርክ’ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሥራ ፈላጊዎች ከአሠሪዎች ጋር ይገናኛሉ።
እዚህ ላይ ያሉ ሥራዎችን “እሠራቸዋለሁ ብዬ ካሰብኩ ፕሮፖዛል እልክላቸዋለሁ። አሪፍ አድርጌ መሥራት እንደምችል ያመኑበት ሰዎች ያናግሩኛል” ሲል ይጠቅሳል ናትናኤል።
ናትናኤል የመጀመሪያው ሥራውን ያገኘው ከለንደን ነበር።
እዚያ ያለ አንድ ደንበኛ በድረገጹ አማካኝነት አጫጭር ቪዲዮዎችን ‘ኤዲት’ የሚያደርግለት ሰው ሲፈልግ ነበር።
ናትናኤል ይህንን ሥራ መሥራት እንደሚችል አመነ።
ከሰውዬው ጋር ተጻጻፉ፣ ሥራውን መሥራት እንደሚችል አሳመነው።
ሥራው ደንበኛው ቀርጾ የላከውን የማስተማሪያ ቪዲዮ ኤዲት ማድረግ እና ተጨማሪ የምሥል መረጃዎችን አካቶ መልሶ መላክ ነው።
■ናትናኤል አፕወርክ፣ ሊንክዲን እና ፋይቨር በተባሉ ድረገጾች አማካኝነት ሥራ ያገኛል
ለዚህ ሥራ መነሻ ገንዘብ አላስፈለገውም። ‘አስተማማኝ’ የሆነ ኮምፒውተርም ሆነ ኢንተርኔት አልነበረውም።
“ዩኒቨርሲቲ ስገባ በገዛሁት በተሰበረ፣ በሚንቀራፈፍ እና አሮጌ በሆነ ላፕቶፕ ነበር የጀመርኩት” ይላል።
ኢንተርኔት ለማግኘት ደግሞ “ዋይፋይ ያላቸው ሰዎች ቤት ወይም ካፌ” ይሄድ ነበር።
ናትናኤል የመጀመሪያውን ሥራ 40 ዶላር ወይም በዚያን ጊዜ በነበረው ይፋዊ ምንዛሪ 2 ሺህ ብር አካባቢ አግኝቶበታል።
እዚህ ጋ፣ ናትናኤል ካገኘው ገንዘብ በላይ “በጣም ጠቅሞኛል” የሚለው ደንበኛው በድረ ገጹ አምስት ኮከብ እና እጅግ አበረታች አስተያየት መስጠቱን ነው።
“‘በጣም ግሩም ሥራ ነው። ሌሎችም ከእርሱ ጋር እንድትሠሩ እመክራለሁ’ የሚል አስተያየት ሰጥቶኛል፥ በጣም ነበር ደስ ያለኝ” ይላል።
በዚህም ገርበብ ያለው የሥራ ዕድል ወለል ብሎ ተከፈተ።
አሁን ከ‘አፕ ወርክ’ በተጨማሪ ‘ፋይቨር’ እና ‘ሊንክዲን’ በተሰኙ ሥራ ማፈላለጊያዎች አማካይነት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ነው።
ከቤቱ መውጣት ሳይጠበቅበት አሜሪካ፣ ስፔን፣ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) እና ዱባይ ያሉ ሥራዎችን እየሠራ ‘ጠቀም ያለ’ ገንዘብ ያገኛል።
ከዚያም አልፎ ሦስት ሰዎችን ቀጥሮ ማሠራት ጀምሯል።
“ባለውለታዬ” የሚለው እና ሰባራ ላፕቶፑን ከፍተኛ ፍጥነት ባላቸው ‘ውድ’ ሦስት ኮምፒውተሮች ቀይሯል።
ልብ በሉ! ይህ ሁሉ የሆነው ዘጠኝ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው።
“ቢዝነሱ የእኔንም የቤተሰቤንም ሕይወት በሆነ ደረጃ ቀይሮታል” የሚለው ናትናኤል “በኦንላይን ሥራ ብቻ ምንም ሳላወጣ፣ ከቤቴ ሳልንቀሳቀስ፣ ከአንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ ብር በላይ ሠርቻለሁ። አሁንም እየሠራሁ ነው። የኢንተርኔት እና የመብራት ችግር ነው እንጂ ከዚህ በላይ እሰራ ነበር” ሲል ገልጿል።
ተከታታይ ሥራ የሚሰጡትን ደንበኞችንም አፍርቷል።
“አንድ ደንበኛዬ ሀበሻ ነው ከዩኬ መጥቶ ቤተሰቤን ጠይቋል። በርቱ ብሎን ሄዷል። አሁንም አብረን እየሠራን ነው” ይላል።
በድረገጾቹ አማካኝነት ቪዲዮ ኤዲትንግ፣ ግራፊክስ ዲዛይን እና ተንቀሳቃሽ ካርታ (map animation) የሚያሠሩ ደንበኞችን እያገኘ ከ5 እስከ 1 ሺህ ዶላር ያገኛል።
የሚገርመው፣ እነዚህን ሥራዎች በሙሉ ዩቲዩብ እየተመለከተ የተማራቸው ናቸው።
ናትናኤል “በኦንላይን ገንዘብ ለመሥራት አንድ ስልክ በቂ ነው” ይላል።
“ባለን ካልሠራን ቢኖረንም አንሠራም። ባለን መጀመር አለብን። ስንጥር ነው ፈጣሪ የሚጨመረው። በፊት ዋይፋይ ለማስገባት አቅም አልነበረኝም. . . ዋይፋይ ያለበት ቤት እየሄድኩ፣ ኢንተርኔት ያለበት ካፌ እየሄድኩ ነበር የምሠራው” ሲል አክሏል።
በእነዚህ ሥራ ማፈላለጊያዎች አማካኝነት “ኮምፒውተር ሳያስፈልገን በቀላሉ መሥራት የምንችላቸው ብዙ ሥራዎች” እንዳሉም ይናገራል።
ለአብነት፣ አንዳንድ ሰዎች አጫጭር ድምጾች (voice over) እንዲነበብላቸው ድረገጾቹ ላይ ሰው ያፈላልጋሉ።
ለዚህ ሥራ የሚያስፈልገው ድምጽ የሚቀርጽ ስልክ ብቻ ነው።
“የቀረጽነው ድምጽ ጥሩ ባይሆን እንኳን [ድምጹን] ማስተካከል የሚችሉ ነጻ ድረገጾች (ዌብሳይቶች)” እንዳሉ ይጠቅሳል።
ሌሎች ደንበኞች ደግሞ መረጃ የሚያሰባስብላቸው ሰው ሊፈልጉ ይችላሉ።
ስልክ እና ኢንተርኔት ያለው ሰው መረጃዎችን ከኢንተርኔት ላይ እየፈለገ ማስገባትም (Data entry) በቀላሉ ሊሠሩ ከሚችሉ ሥራዎች አንዱ ነው።
‘የኦንላይን ሥራ’ እና አጭበርባሪዎች
ናትናኤል መጀመሪያ ‘በኦንላይን’ ገንዘብ የሠራው በ‘አፕ ወርክ’ ነው። አሁን ከዚያም አልፎ ‘በፋይቨር’ እና ‘ሊንክድኢን’ አማካኝነት ሥራ ያገኛል።
‘አፕወርክ’ በአውሮፓውያኑ 2013 አሜሪካ፣ ካሊፎርኒያ ውስጥ የተጀመረ ሥራ አገናኝ ድረገጽ ነው።
‘ፋይቨር’ ደግሞ በ2010 እስራኤል፣ ቴላቪቭ ውስጥ የተመሠረተ ሲሆን፣ በ10 ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሥራ እና ገንዘብ አስገኝቷል።
ከ20 ዓመት በፊት የተጀመረው ‘ሊንክዲን’ም እንዲሁ።
በእነዚህ ድረገጾች በትርፍ ወይም በሙሉ ጊዜ የሚሠሩ በሺዎች የሚቀጠሩ ሥራዎች አሉ።
መሥራት የሚፈልጉ ሰዎች ክህሎታቸውን፣ የሥራ ልምዳቸውን እና ሌሎች መረጃዎችን በእነዚህ ድረገጾች አማካኝነት ይጭናሉ።
ተመሳሳይ ገጾቹ ላይ ማሠራት የሚፈልጉ ግለሰቦች ወይም ኩባንያዎችም ይገኛሉ።
አሠሪዎች ከሚያወጡት ማስታወቂያ ስር ሥራ ፈላጊዎች የሚያስከፍሉትን የገንዘብ መጠን ያስቀመጣሉ።
አሰሪው የሥራ ፈላጊውን መረጃዎች እና የገንዘብ መጠን አይቶ ‘ያዋጣኛል’ ላለው ሥራውን ይሰጣል።
ይህንን የመሰሉ በርካታ ድረገጾች አሉ። ችግሩ ሁሉም ትክክል አይደሉም አንዳንዶቹ ለቀማኛ አሳልፈው ይሰጣሉ። አንዳንድ አጭበርባሪዎች ደግሞ በትክክለኞቹ ገጽ በኩል ሊመጡ ይችላሉ።
ናትናኤል በምርቃቱ ወቅት ከእናቱ ጋር
አጭበርባሪዎች በሥራ ድረገጾች አማካኝነት ሥራ ፈላጊዎችን ዒላማ እንደሚያደርጉ ቢቢሲ በአንድ ወቅት ያገኘው መረጃ አመልክቷል።
ሊንክንዲን ሐሰተኛ ‘አሰሪ ነን ባዮችን’ የሚያስወግደበት አሠራር መዘርጋቱንም ጠቅሷል።
ያኔ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቅጥር እና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ አጭበርባሪዎች በብዙ መንገድ እንደሚመጡ አስረድተዋል።
ሁሉም ባለሙያዎች ሥራ ፈላጊዎች ሥራ ከመጀመራቸው አስቀድሞ ‘ቀጣሪ ነን’ የሚሉ ኩባንያ ወይም ግለሰቦች ትክክለኛ መሆናቸውን እንዲያጣሩ ይመክራሉ።
የናትናኤልም ሀሳብ ተመሳሳይ ነው።“የምንሠራበትን ዌብሳይት ትክክለኝነት ሳናረጋግጥ ሥራ ከጀመርን እና ችግር ከገጠመን ተስፋ እንድንቆርጥ እና ሌሎችን እንዳናምን ነው የሚያደርገን” ይላል።
ቀጥሎም “ማንኛውንም ሥራ ከመጀመራችን በፊት 10 ደቂቃ ወስደን [ሰለ ድረገጹ] ብናጣራ ሁሉንም ማወቅ እንችላለን። ያየነውን ሁሉ ማመን የለብንም፤ ማጣራት ይኖርብናል” ሲል ገልጿል።
■“የኦንላይን ሥራ ትጋት ይፈልጋል”
ናትናኤል በኦንላይን የሚሠሩ ሥራዎች ጥሩ ገንዘብ ቢሠራባቸውም ትዕግሥት እንደሚፈልጉ ይገልጻል።
“የኦን ላይን ሥራ ትጋት ይፈልጋል። አሁን እኔ ከጓደኞቼ ጋር የምዝናናበትን ጊዜ ቀንሼ፣ ከቤተሰቤ ጋር በደንብ ጊዜ ማሳለፍ ብፈልግም እሱንም ቀነስ አድርጌ፣ እንቅልፌን ቀነስ አድርጌ ነው የምሠራው። የወደፊቱን ለማሳካት ያለኝ አማራጭ ትጉህ መሆን ብቻ ነው” ይላል።
ቀጥሎ “በምንም ነገር ተስፋ አልቆርጥም” ሲል ጨምሯል።
ለናትናኤል ትጋት እና ተስፋ አለመቁረጥ መገለጫዎቹ የሆኑት ግን ከዚህ ሥራም ቀደም ብሎ ነው።
ወጣቱ ቤተሰቦቹን መደገፍ የጀመረው እንደሚጠበቀው የምረቃ ጋወን ካጠለቀ፣ መነሳነስ ካዞረ እና ሥራ ከጀመረ በኋላ አልነበረም።
*የ26 ዓመቱ ናትናኤል በኮምፒውተር ሳይንስ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመርቋል።
ያኔ ከቤተሰብ የሚላክለት ገንዘብ አልነበረም። በታቀራኒው እርሱ ወደ አዲስ አበባ ገንዘብ ይልካል - ወደ ቤተሰቦቹ።
በተለይ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሳለ አባቱ በጠና ከታመሙ በኋላ ቤተሰቡን ‘ቀጥ አድርጎ’ አስተዳድሯል።
አራት ወንድሞቹን አስተምሯል።
በሚገኘው ገንዘብ የአባቱን ሕክምና፣ የቤት አስቤዛ፣ የእህት እና ወንድሞቹ የትምህርት ቤት ወጪ ይሸፍን እንደነበር ይናገራል።
ዩኒቨርሲቲ እየተማረ፣ አዳራሽ ተከራይቶ ከ20 እስከ 30 የሚሆኑ ሰዎችን ዳንስ እያሠለጠነ ገንዘብ ያገኝ ነበር።
ሲመሽ ደግሞ ‘በዲጄነት’ ባሕር ዳር የሚገኝ ዕውቅ ሪዞርት ውስጥ ይሠራ ነበር።
ቅዳሜ እና እሁድ ፎቶ ቤቶች ሄዶ የሠርግ ቪዲዮዎችን ኤዲት ያደርግ ነበር። እየተማረ ይህንን ሁሉ እየሠራ በወር ከ8 እስከ 10 ሺህ ብር ያገኝ እንደነበር ጠቅሷል።
ከዚያ ቀደም ብሎ ከአባቱ የተማረውን የእንጨት ሥራ ሠርቷል። ከዚያ በፊት ደግሞ በአስራዎቹ እድሜ ላይ እያለ ዲሽ ይጠግን ነበር።
አባቱ ከወራት በፊት ሕመማቸው ጥንቶ አርፈዋል። አሁን ሙሉ በመሉ ቤተሰቡን የማስተዳደር ኃላፊነትን ወስዷል።
በሥራዎቹ ያዳበረው ትጋት እና ተስፋ አለመቁረጥ ወደፊት ሩቅ ለሚያስብበት ‘የኦንላይን ቢዝነስ’ እጅግ እንደጠቀመው ይናገራል።
bbc
30/11/2023
የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተመሳሳይ ጾታ እንቅስቃሴዎች ላይ እገዳ ጣለ
**********************
የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት “ዓለም አቀፍ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት የአደባባይ እንቅስቃሴ” ጽንፈኛ ድርጅት ነው በማለት እንቅስቃሴዎቹ የተከለከሉ ናቸው ሲል አወጀ።
በሩሲያ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት እውቅና የለውም። በሩሲያ ትዳር ማለት የወንድ እና የሴት ጥምረት ማለት ስለመሆኑ ትርጉም ለመስጠት የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ከሦስት ዓመታት በፊት ተቀይሮ ነበር።
ይህ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በይፋ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የተመለከቱ እንቅስቃሴዎችን የሚከለክል ሲሆን፣ ሕጉን የሚተላለፍ በእስር ይቀጣል።
ውሳኔው በአገሪቱ የሚገኙ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎችን እና ደጋፊዎቻቸውን አላስደሰተም።
ባለፈው ዓመት የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ መሆኑን በይፋ የገለጸው የሴንት ፒተርስበርግ ምክትል ከንቲባ ሰርጌይ ትሮሺን ውሳኔው በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪን ማኅብረሰብ ውስጥ የእስር ስጋት መፍጠሩን እና ሩሲያን ጥለው የሚወጡ ዜጎች መበራከታቸውን ተናግሯል።
“ይህ ማለት መንግሥት የተመሳሳይ ጾታ አቀንቃኝ ነው ብሎ የሚያስበውን ማንኛውም ሰው ረዥም የእስር ጊዜ ሊጠብቀው ይችላል። ይህ ጭቆና ነው። ትልቅ መደናገጥ አለ። ሰዎች በፍጥነት ከአገር እየወጡ ነው። ...ከራሳችን አገር ለመሰደድ እየተገደድን ነው” በማለት ሐዘኑን እና ስጋቱን ገልጿል።
እራሱን የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ማኅብረሰብ አካል አድርጎ የሚቆጥረው ማክሲም ጎልድማን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ከሩሲያ ወጥቷል።
“በራሴ አገር እንደተገፋሁ ይሰማኛል። ...ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዳለን ነው የምናስበው። ሥልጣን ላይ የምናወጣቸው ሰዎች ሊጠብቁን ይገባቸዋል። ይሁን እንጂ በተቃራኒው ነው እየሆነ ያለው። እየቀጡን ነው። ...በኃይል ከአገር እያስወጡን ነው” ብሏል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሩሲያ መንግሥት በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን እና በእንቅስቃሴያቸው ላይ ጠንከር ያለ እርምጃን እየወሰደ ይገኛል።
እአአ በ2013 ላይ “ከተለመደው ውጪ ስላለ ጾታዊ ግንኙነት የሚደረግ ፕሮፖጋንዳን” የሚከለክል ሕግ ወጥቶ ነበር።
የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያንን የሚያመለክቱ ይዘቶች ከመጽሐፍት፣ ከፊልሞች፣ ከማስታወቂያዎች እና ከቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ተሰርዘዋል።
የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን እና እንቅስቃሴያቸው በሕግ እንዲገደብ በመከራከር የሚታወቁት የአገሪቱ ምክር ቤት አባል ቪታሊ ሚሎኖቭ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ከግል ጾታዊ ፍላጎታቸው በላይ የምዕራባውያን ፍላጎት ማስፈጸሚያ ድብቅ አጀንዳዎች አሏቸው ይላሉ።
“የራሳቸው ዓላማ አላቸው። የፖለቲካ ቅርጽ ኖሯቸው እና ዓላማ ኖሯቸው እንደ የፖለቲካ ኃይል ነው የሚንቀሳቀሱት። ...የትኛውም የተመሳሳይ ጾታ እንቅስቃሴ እንዲገደብ እንፈልጋለን። አያስፈልጉንም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ሥር በሩሲያ ጾታዊ ግንኙነቶችን በተመለከተ ወግ አጥባቂ አስተሳሰቦች የሰረጹ ሲሆን፣ “የተለመዱ የቤተሰብ እሴቶችን” ማስጠበቅ የሚሉ አመለካከቶች ተጠናክረዋል።
የሩሲያ መንግሥት ባለሥልጣናት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት እንቅስቃሴዎች ከምዕራባውያን የተቀዱ እና ለአገሪቱ አደጋን የሚደቅኑ አድርገው ይገልጻሉ።
Bbc
30/11/2023
#አስፈሪ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ፈጠራ መጥቷል አሉ!
*******************
አንደኛውን ዓለማቀፍ ዜና አይተናል። የሮኬትና የህዋ ቴክሎጂ ነው። ሁለተኛው ዜናስ ምንድነው? ግን ምን ዋጋ አለው? ትልቁ ዜና እንደገና ተመልሶ ተሽሯል።
“ሳም አልትማን ተባረረ” ተብሎ ቅዳሜ ዕለት ተዘገበ።
ሮብ ዕለት ደግሞ ወደ ቦታው ተመልሷል ተብሎ እንደገና እንደ ጉድ ተወራ።
ለመሆኑ አልትማን ማለት ማን ነው?
የ “OpenAI” ዋና መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ነው። የዓለማችን ቁጥር አንድ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ተቋም ነው-Open AI::
እንግዲህ፣ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ላይ የበላይትን የተቆጣጠረ አገር፣ የዓለማችን ገዢ ይሆናል ብለዋል- የራሺያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን።
ቢያንስ ቢያንስ በዚህ ጉዳይ ላይ የአሜሪካ፣ የአውሮፓ፣ የቻይና መንግስታትም ጭምር በፑቲን ንግግር ይስማማሉ።አስገራሚው ነገር፣ በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ቴክኖሎጂ ላይ በቀዳሚነት እየመሩና እየገሰገሱ የሚገኙ ተመራማሪዎችና የፈጠራ ሰዎችም፣ ቴክኖሎጂው እጅግ ኃያል ከመሆኑ የተነሳ፣ የጥቅሙ ያህል አደጋውም እጅግ አስፈሪ እንደሆነ ይናገራሉ።
ቴክኖሎጂው ደግሞ በከባድ ፍጥነት እየተሻሻለ እየተራቀቀ ነው።
በዚህ መሀል ነው አዲስ ተጨማሪ ግኝት፣ እጅግ የተራቀቀ አዲስ የፈጠራ ውጤት እንደተገኘ ከሳምንት በፊት ሐሙስ ዕለት የተገለፀው። Open AI ነው የፈጠራው ባለቤት።ምን ዓይነት ፈጠራ እንደሆነ በግልፅ አልተነገረም። ነገር ግን፣ በራሱ ጊዜ የሒሳብ ስሌቶችንና ቀመሮችን መገንዘብ የሚችል ቴክኖሎጂ ባተጠበቀ ፍጥነት እንደተፈጠረ ተጠቅሷል። አዲሱ ፈጠራ ብዙዎችን እንዳስገረመና እንዳስደነገጠም በዓለማቀፍ የዜና አውታሮች ተዘግቧል።
አግራሞት፣ ድንጋጤና ፍርሀት ውስጥ ለውስጥ ሲብላሉ በማግስቱ ፈነዱ። የድርጅቱ መሪዎች ተወዛገቡ።
ከሰው ቁጥጥር ውጭ የሆነ፣ እንደ ተርሚኔተር ዓይነት ቴክኖሎጂ የሚመጣበት ጊዜ ተቃርቧል የሚል ስጋት የተፈጠረው፣ Open AI ውስጥ ጭምር፣ ቴክኖሎጂውን በሚያውቁ በባለሙያዎች ዘንድም ነው ተብሏል።
የውዝግቡ ማቀጣጠያ ይሄው ነው።…ስራ አስኪያጁ ተባረረ፤ ተመልሶ ቦታውን ያዘ የሚለው ዜና ትልቅ ዓለማቀፍ ወሬ ለመሆን የቻለውም፣ ከአዲስ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ፈጠራ ጋር በተያያዘ ሰበብ ነው። ሰውን ከምድረ-ገፅ የሚያጠፋ ቴክኖሎጂ ሊመጣ ይችላል የሚል ነው ስጋታቸው። ምን ሆነዋል እዚህ ሰዎች! ለዚያውም ባለሙያዎቹ፣ የቴክኖሎጂው ፈጣሪዎች ናቸው ይህን የሚናገሩት።
ለማመን ይከብዳል። ለክፉም ለደጉም፣ አዲስ ነገር እየመጣ እንደሆነ ግን አትጠራጠሩ።
Yohanes
04/11/2023
#የህፃናት የአንገት እጢ ሆርሞን ማነስ (congenital hypothyroidism)
■■■■■■■♤♤♤♤
አንገት አካባቢ የሚገኘው ታይሮድ እጢ የሚያመነጨው ሆርሞን ለአእምሯችን እድገት እና የተለያዪ የሰውነት ክፍሎቻችን ስራቸውን በትክክል እንዲሰሩ እገዛ በማድረግ የሚጫወተው ሚና ለህወታችን ወሳኝ ነው። በተለይ ለህፃናት የአእምሮ /አንጎል መዳበር/እድገት በመጀመሪያው ሁለት አመት ወሳኝ አስተዋፆ እንዳለው ይታወቃል።
ለሆርሞኑ ማነስ ምክንያቶች
1. ሆርሞኑን የሚያመርቱ ኢንዛየም ችግር ካለ
2. ሆርሞኑን ለማምረት በጣም ወሳኝ የሆነው አይውዲን(iodine) እጥረት ካጋጠመ
3.የሆርሞኑን አመራረት ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ መድሃኒቶች እናቶች በእርግዝና ወቅት ወይም ጡት ሲያጠቡ ከወሰዱ
4. ሆርሞኑን የሚያመርተው ዕጢ አካለ ስሪት ችግር ካለ(thyroid gland dysgenesis)
5. ከእናቶች የሆርሞን መብዛት ጋር ተያይዞ የሚመረተው ፀረ-እንግዳ አካል (TSH -receptor blocking antibodies) ከማህፀን ወደ ፅንስ ከተላለፈ
በእኛ ሃገር በዋናነት በተለይ በአዎቂዎች ላይ የሆርሞን ማነስ ችግር ከአይውዲን እጥረት ጋር ተያይዞ ሊከሰት ይችላል።
ከ80-85%የሚሆነው የህፃናት ሆርሞን ማነስ (congenital hypothyrodism) የሚከሰተው ከዕጢው አፈጣጠር አካለ ስሪት ችግር (thyroid gland dysgensis) ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል።
በሁለተኛ ደረጃ እንደምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ ሆርሞኑን ለማምረት የሚያገለግለው የኢንዛዬም ችግር (thyroid dyshormonogensis)ነው።
በሶስተኛ እንደምክኒያት የሚጠቀሱት ደግሞ የአይውዲን እጥረት :እናቶች ለሆርሞን መብዛት ህክምና የሚወስዱት መድሃኒት ወይም ከእናት ወደ ፅንስ የሚተላለፈው ፀረ -እንግዳ አካል(TSH receptor blocking antibodies) ሊሆኑ ይችላሉ።
ምን እናድርግ?
1.የጨቅላ ህፃናት የሆርሞ ቼክ አፕ(neonatal screening) ማድረግ
2.ከተወለዱ በኋላ የሆርሞን ክትትል(TSH,T3,T4) በቀጠሮ ማየት(መጀመሪያ ላይ ምንም አይነት የምርመራ ችግር ባይኖርም ተከታታይ ምርመራዎች ለተወሰኑ ወራት ያስፈልጋል)።
3.የሆርሞን ማነስ ችግር ካለ መድሃኒት ቶሎ ማስጀመርና ክትትል ማድረግ(መድሃኒቱን ቢያንስ የአንጎል መዳበርና እድገት እስከሚጠናቀቅ መውሰድ ይኖርባቸዋል)።
ለሆርሞን ማነስ ህክምናው ካልተደረግ ምን ይፈጠራል?
ለአእምሮ ውስንነት(Intellectual disabilities) ይጋለጣሉ።
ውጫዊ የፊት አካባቢ የመልክ ችግር መፈጠር ይኖራል።
የጡንቻ መልፈስፈስ እና የአመጋገብ ችግር እንዲሁም የእንግልፍ መብዛት ይገጥማቸዋል።
በመጨረሻም የቤተሰብ እና የበሽታው ተጠቂዎች የኑሮ መዛባት ይከሰታል።
በእርግዝና ወቅት የአንገት ዕጢ የሆርሞን ማነስም ይሁን መብዛት ከገጠምዎ ለሚወልዱት ልጅ ሲሉ ወደ ጤና ተቋም በጊዜ በመምጣት እና ክትትል በማድረግ የወደፊት የልጅዎን ህይወት መታደግ ያስፈልጋል
04/11/2023
#የአገር ጽዮናዊነት ምንድን ነው?
***************
ጽዮናዊነት በአውሮፓ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው። ፍልስጥኤም በምትባለውም ምድር የአይሁድ አገርን መመሥረት ዋነኛ ግቡ ነው። ይህ እንቅስቃሴ የአይሁዳውያን የጥንት ርስት ናት የሚሏትን የአይሁዳውን አገር የሆነች እስራኤል ፍልስጥኤም ተብሎ በሚታወቀው መሬት የመመሥረት ፍላጎት የነበረው ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ፍልስጥኤም ለሁለት ተከፍላ የአይሁዶች እና የአረቦች የተናጠል አገራት አንዲመሠረቱ ሃሳብ አቀረበ። በአውሮፓውያኑ 1948ም እስራኤል በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ በአገርነት መመሥረቷ ታወጀ።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ከቀያቸው እና ከቤታቸው ተፈናቀሉ። ከዚያም በኋላ እ.አ.አ በ1967 የተደረገውን የስድስቱን ቀን ጦርነት ተከትሎ የፍልስጥኤም ግዛቶች የሚባሉትን ዌስት ባንክን እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን እስራኤል በኃይል ተቆጣጥራ ትገኛለች። ባለፉት አምስት አስርት ዓመታትም በነዚህ ግዛቶች የአይሁዶች የሰፈራ መንደሮችን አቋቁማለች። 700 ሺህ የሚቆጠሩ አይሁዳውያን በእነዚህ ስፍራዎች አስፍራለች።
የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት እስራኤል በቁጥጥሯ ስር ባሉ ግዛቶች የሰፈራ መንደሮችን ማቋቋሟ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጻረር እና ሕገወጥ ነው ሲሉ ይጠሩታል። የእስራኤል መንግሥት ምሥረታ በፍልስጥኤም የሚኖሩ አረቦችን መብት የነፈገ መሆኑን በመጥቀስ ፍልስጥኤማውያን እንዲሁም ሌሎች አረቦች ይቃወሙታል።
የጽዮናዊነትን እንቅስቃሴ የሚያቀነቅኑ አካላት እስራኤል እንደ አይሁድ ግዛትነቷ ጥበቃ ሊደረግላት እንዲሁም ልትስፋፋ ይገባል ብለው ያምናሉ። አንዳንድ ጽዮናውያን እስራኤል ካላት ግዛት በተጨማሪ ሌሎች ግዛቶችንም የመቆጣጠር መብት አላት ብለው የሚከራከሩ ሲሆን፣ ሌሎች በዚህ ሃሳብ አይስማሙም። አብዛኛው አይሁዳውያን ጽዮናውያን ቢሆኑም፣ ጥቂቶች በፖለቲካዊ እና በሃይማኖታዊ ምክንያቶች ጽንሰ ሃሳቡን ይቃወማሉ። አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች ጽዮናዊነትንም ማቀንቀን ይችላሉ።
Click here to claim your Sponsored Listing.
Category
Contact the public figure
Website
Address
Awash Town
Awash